የዳያስፖራው ማህበረሰብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የዳያስፖራው ማህበረሰብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
ውይይቱ ዳያስፖራው ማህበረሰብ በልማት እና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
በውይይቱ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት፣ ከሌሎች ተቋማት የተወከሉ የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እንደተናገሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ ከ95 በመቶ በላይ ደርሷል።
ግድቡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የዳያስፖራው ተሳትፎ የላቀ ሚና መጫወቱን ጠቅሰው ዳያስፖራው በዲፕሎማሲ፣ በቦንድ ግዥና ሌሎችም መስኮች ያበረከተው ድጋፍ ወሳኝ እንደነበር ተናግረዋል።
ግድቡ አሁንም ቀሪ ስራዎች ያሉት በመሆኑ የዳያፖራው ማሕበረሰብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ ዳያስፖራው በሀገሩ ልማት ላይ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር እየሰራ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የዳያስፖራ አደረጃጀቶችን ማጠናከር ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል።