የለውጡ መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያን ብልፅግና እና ብሔራዊ ጥቅም የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ሥራዎችን አከናውኗል - ዶክተር ለገሠ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
የለውጡ መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያን ብልፅግና እና ብሔራዊ ጥቅም የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ሥራዎችን አከናውኗል - ዶክተር ለገሠ ቱሉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያን ብልፅግና እና ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ሥራዎች ማከናወኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ ገለጹ።
ሚኒስትሩ በስድስት ዓመታት የለውጥ ሥራዎች፣ በሰላም ስምምነቱና በበጋ ልማት ስራዎች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሠላም የሠፈነባት ኢትዮጵያ የራሷን ልማት እውን ከማድረግ በላይ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ተሰሚነቷን ከፍ ለማድረግና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እንደምትችል ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጥ መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ምህዳር ለመፍጠር ዘርፈብዙ ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
ለአብነትም በፖለቲካው ረገድ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዘጋጀቱን፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙን፣ የዴሞክራሲ፣ የፍትህና የፀጥታ ተቋማት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን አንስተዋል።
በዚህም የለውጡ መንግሥት አካታች ህብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ የፌደራሊዝም ሥርዓት በተጨባጭ መትከሉን ገልጸዋል።
መጋቢት ወር የኢትዮጵያ የመለወጥ ፍላጎት እውን የሆነበትና ተጨባጭ የብልፅግና ጉዞ የተጀመረበት ነው ብለዋል።
በኢኮኖሚው መስክ አመርቂ እድገት መመዝገቡን የሀገሪቱ ሀብት በእጥፍ መጨመሩን፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መሻሻሉን፣ የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እድገት ውጤት እያስገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በበጋ መስኖ ስንዴ እና በአረንጓዴ አሻራ የተገኙ ሥኬቶች የሀገርን ገፅታ የቀየሩ ስለመሆናቸውሞ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን የማፍረስ የውስጥና የውጭ ሴራዎች በበሳል አመራርና በብርቱ ትግል ስለመክሸፋቸውም ነው ያነሱት።
የለውጡ መንግሥት በዲፕሎማሲው መስክም የኢትዮጵያን ተሰሚነት የጨመሩ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን ያስጠበቁ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የውጭ ግንኙነት ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።