በሀገሪቱ የተከናወነው ሪፎርም የስርአተ ትምህርት ለውጥና ጥራትን ለማምጣት መደላድል እየፈጠረ ነው- የትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ የተከናወነው ሪፎርም የስርአተ ትምህርት ለውጥና ጥራትን ለማምጣት መደላድል እየፈጠረ ነው- የትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተካሔደው ሪፎርምና የስርአተ ትምህርት ለውጥ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የሚያስችል መደላድል እየፈጠረ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተካሔዱ የለውጥ ስራዎች የትምህርት ጥራትን ለማምጣት መሰረት እየጣሉ መሆናቸው ይታወቃል።
የለውጥ ስራው በየደረጃው የነበረውን የትምህርት ጥራት ችግር ለማስተካከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተም ይገኛል ።
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የስርዓተ ትምህርት ፕሮግራሞች ዴስክ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ነገው፤ለኢዜአ እንዳሉት በከፍተኛ ትምህርት ዙሪያ የሚታየውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመፍታት ጥናቶች ተካሒደዋል።
በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ ፕሮግራሞች ተመሳሳይነት፣የተገቢነትና የጥራት ችግር እንዳለባቸው በጥናቱ ተመላክቷል ነው ያሉት።
በዚሁ መሰረት ተቋማቱ የሚሰጧቸውን የትምህርት መስኮች እንዲፈተሹና እንዲከለሱ መደረጉን ጠቁመዋል።
በተለይም በርካታ የትምህርት ተቋማት ተመሳሳይነት ያላቸው መርኃ ግብሮችን የሚያስተምሩ መሆኑ በመለየቱ የነበሩትን ክፍተቶች በመፈተሽ ወደ አንድ እንዲጠቃለሉ መደረጉን ጠቁመዋል።
ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ 150 የሚደርሱ የትምህርት ፕሮግራሞችን ለመጀመር ጥያቄ ማቅረባቸውን በማስታወስ በርካቶቹ ይዘታቸው ተመሳሳይ በመሆኑ 55 የሚሆኑት ብቻ ተቀባይነት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም ተቋማቱ የትምህርት መስኮችን ከማብዛት ይልቅ ጥራት በሚያመጡ ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
ጥናቱ ዩኒቨርሲቲዎች በተልዕኮና በትኩረት መስክ ላይ እንዲሰሩ በማድረጉ የተገቢነትና የጥራት ችግሮችን እየፈቱ እንዲሄዱ እያስቻላቸው መሆኑንም አብራርተዋል።
ጥራትን ከሚያስጠብቁ ዋና ዋና ተግባራት አንዱ ደግሞ የፈተና አሰጣጥን ማዘመን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ አጠቃላይ የፈተና አሰጣጥ ስርአትን ለመቀየር በመቻሉ ብቃት ያለው ተማሪ ለማፍራት መደላድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።
በተለይም ለመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና መሰጠት መጀመሩ ተማሪው በተገቢው መንገድ ትምህርቱን እንዲከታተል ፣እንዲያነብና ራሱን በበቂ ደረጃ እንዲያዘጋጅ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ለውጡን ተከትሎ የትምህርት ስርዓቱ እንዲቀየር መደረጉ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚበጅና ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት መንገድ መክፈቱን ጠቅሰዋል።