በአማራ ክልል ፅንፈኛውን ቡድን ተቀላቅለው የነበሩ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች ተሃድሶ ወስደው ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለዋል - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ፅንፈኛውን ቡድን ተቀላቅለው የነበሩ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች ተሃድሶ ወስደው ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለዋል - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ፅንፈኛውን ቡድን ተቀላቅለው የነበሩ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች ተሃድሶ ወስደው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ በስድስት ዓመታት የለውጥ ሥራዎች፣ በሰላም እና የህግ ማስከበር እርምጃዎች እንዲሁም በበጋ ልማት የተከናወኑ ስራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
መንግሥት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን በሰላማዊ ንግግር ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር የህግ ማስከበር ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል በፅንፈኛው ቡድን ላይ በተጀመረው የህግ ማስከበር ሥራ ክልሉ ከሞላ ጎደል ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሱን አንስተዋል።
የክልሉን የፖለቲካና የፀጥታ አመራር በተዋረድ በአዲስ መልኩ በማደራጀት ወደ ስራ መገባቱንም ነው ያነሱት።
በልዩ ልዩ አሳሳች መንገዶች ፅንፈኛውን ቡድን ተቀላቅለው የነበሩ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች ተሃድሶ ወስደው ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውንም ተናግረዋል።
ከ10 ሺህ ያላነሱ የቀድሞ የልዩ ኃይል አባላት ተሃድሶ ወስደው የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ክልሉ ወደተሻለ ሠላም መመለሱን ገልጸው ህብረተሰቡም የህግ ማስከበር ስራውን እያገዘና ለሰላም ዘብ እየቆመ ነው ብለዋል።
ፅንፈኛው ቡድን የተወሰደበትን እርምጃ መቋቋም አቅቶት ወደ ዝርፊያ፣ ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ የማድረስ ስራውን ወደማስተጓጎልና ሌሎች ተግባራት መሠማራቱን ተናግረዋል።
የፌደራልና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በቡድኑ ላይ እርምጃቸውን አጠናክረው በመቀጠል በአጭር ጊዜ ተልዕኳቸውን እንደሚያጠናቅቁም ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል ውስን አካባቢዎች በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ሽብር ቡድን ላይም ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ ሲሆን አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ወደ ሰላም እየመጡ ነው ብለዋል።
የተፈጠረውን የሰላም ምቹ ሁኔታ መሠረት በማድረግ የልማት ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል የቆዩ ዜጎችም ወደቀያቸው እየተመለሡ ነው ብለዋል።