የኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል አሰባሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል አሰባሰበ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ባለሀብቶች 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማሰባሰቡን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ጥላሁን እስማኤል የካፒታል ማሰባሰቢያውን ማጠቃለያና የገበያውን ደንብ አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ገበያው ለመሰብሰብ ያቀደው 631 ሚሊዮን ብር ሲሆን የተሰበሰበው ካፒታል 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ከዕቅዱ በ240 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸው 48 በፋይናንስና ከፋይናንስ ዘርፍ ውጪ ባሉ መስኮች የተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶች ተሳትፈዋል ብለዋል።
ገበያው ጥቅምት 2016 ዓ.ም የመንግስትና የግል አጋርነትን መሰረት በማድረግ የተቋቋመ መሆኑንም አንስተዋል።
ካፒታል በማሰባሰብ ሂደቱ የታየው ከፍተኛ ፍላጎትና ርብርብ ኢትዮጵያ እያካሄደች ላላው የፋይናንስ ዘርፍ ልማትና የኢኮኖሚ ለውጥ አዲስ የስኬት ጉዞ መሆኑን አብራርተዋል።
ገበያው አዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚፈጥር፣ የስራ ፈጣሪነትን የሚያበረታታና በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ዘላቂ ልማትን የማስፋት አላማን ያነገበ መሆኑንም እንዲሁ።
ገቢያውን ወደ ስራ ለማስገባት ወሳኝ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ህገደንብ ለህዝብ የማሳወቅና የቴክኖሎጂ የመሰረተ ልማቶችን የማጠናቀቅ ስራዎች እየተካሔዱ መሆኑንም ገልጸዋል።