ቀጥታ፡

የሦስት ተርባይኖች የጥገና ሥራ ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም ተከናወነ

አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 26/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ካሉት አራት ተርባይኖች የሦስቱን ጥገና ሥራ ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም ማከናወኑን አስታወቀ።

በጣቢያው የጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ስዩም ኃይሉ እንደገለጹት ከ2013 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለተወሰኑ ወራት የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ከብሔራዊ የኃይል ቋት ውጪ ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል።

ይሁንና አካባቢው ወደ ሠላም ከተመለሰ በኋላ ጣቢያው ካሉት አራት ተርባይኖች ውስጥ የሦስቱን ተርባይኖች ጥገና ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም መከናወኑን ኃላፊው ገልጸዋል።


 

ቀሪው ተርባይንም ተፈቶ የጥገና ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ስዩም ጥገናቸው ከተጠናቀቁት ሦስት ተርባይኖች መካከል አንዱ በንዝረት ፍተሻ ላይ በመሆኑ በአሁን ወቅት ጣቢያው በሁለት ተርባይኖች ኤሌክትሪክ እያመነጨ ይገኛል ብለዋል።

ጣቢያው በሙሉ አቅሙ ኃይል ወደ ማመንጨት እንዲገባ የሚያስችሉ የማስተካከያ፣ የቅድመ መከላከልና የጥገና ሥራዎች እንዲሁም ሳምንታዊና ወርሃዊ የፍተሻ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

የጣቢያው የጥገና ባለሙያ የሆኑት አቶ ሚካኤለ ገብረጻዲቅ በበኩላቸው የተርባይንን ጨምሮ ሌሎች የጥገና ሥራዎችን በራስ አቅም እያከናወኑ በመሆናቸው ጊዜንና ወጭን መቆጠብ እንዳስቻለ ተናግረዋል።

የጣቢያውን የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም ማከናወናቸው ሠራተኞች እርስ በእርስ ልምድ የሚለዋወጡበትና አቅማቸውን የሚያጎለብቱበትን እድል እንደፈጠረላቸውም ጠቁመዋል።

ከመለዋወጫ ዕቃ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈታላቸውም መጠየቃቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በ1994 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ ጥቅምት 2002 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 300 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም