የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፡የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ይጀምራሉ።
በመርኃ ግብሩ መክፈቻ ወልቂጤ ከተማ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመራው ወልቂጤ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም ፣ በሁለቱ ሲሸነፍ በሶስቱ አቻ ወጥቷል።
ክለቡ በ12 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ተቀምጧል።
በያሬድ ገመቹ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፣ በሶስቱ ሽንፈት ሲያጋጥመው በሁለቱ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።
ወላይታ ድቻ በ24 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌላኛው የ20ኛ ሳምንት የሊጉ መርኃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀምበሪቾ ዱራሜ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል ፣ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
ንግድ ባንክ በ37 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ሀምበሪቾ ዱራሜ በበኩሉ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፣ በአራቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በጊዜያዊ አሰልጣኙ ብሩክ ሲሳይ የሚመራው ሀምበሪቾ ዱራሜ በ7 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል።
የፕሪሚየር ሊጉ የ20ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ነገ ቀጥሎ ሲውል ኢትዮጵያ ቡና ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ፤ ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የሊጉ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።
መቻል በ39 ነጥብ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ይገኛል።
የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የሃዋሳ ከተማው አጥቂ አሊ ሱሌይማን በ11 ግቦች ሲመራ ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ የፊት መስመር ተሰላፊ ቻርልስ ሙሲጌ በ9 ግቦች ይከተላል።