የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል - አቶ እንዳሻው ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል - አቶ እንዳሻው ጣሰው
ሆሳዕና ፤መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ እንዳሻው ጣሰው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለክልሉ ህዝብ ብሎም ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንችላለን መንፈስን ያላበሰ የጋራ ፕሮጀክት ነው።
ግድቡ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካዊያን አቅም ከተሰባሰበ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ተጨባጭ ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።
የክልሉ ህዝብ የግድቡ ግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሲያደርገው የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ “በህብረትና በአንድነት በመነሳት ታሪክ መስራት እንደሚቻል በተጨባጭ ያሳየ ነው” ያሉት አቶ እንዳሻው፤ የግንባታ ሥራው ወደመገባደድ መድረሱ በህዝቡ ላይ መነቃቃትን መፍጠሩን ተናግረዋል።
አቶ እንዳሻው እንደገለጹት፤ ክልሉ በአዲስ መልክ ሲደራጅ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በማቋቋም ድጋፉን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የክልሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ተክሌ አሼቦ በሰጡት መግለጫ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ “ኢትዮጵያዊያን በአብሮነትና በአንድነት አሻራቸውን ያሳረፉበት ብሔራዊ ኩራታችን ነው” ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ ያለ ልዩነት በአንድ ሀሳብ ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዢ፣ በዓይነትና በጉልበት እያደረገ ያለው ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ህዝቡ እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ከ410 ሚሊዮን 762 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም አቶ ተክሌ አስታውቀዋል።
በተለይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ "በህብረት ችለናል" በሚል መርህ በየአካባቢው በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ድጋፉ መጠናከሩንም ገልጸዋል።
ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረግ ድጋፍ ቁጠባን ከማበረታታት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለውም አቶ ተክሌ ተናግረዋል።