ቀጥታ፡

የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡-  የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አባሶ ተፈራርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ከ2016 በጀት አመት መጀመሪያ አንስቶ እስከ አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ከ 22 ሺህ በላይ የትራፊክ አደጋዎች ደርሰዋል፡፡

በነዚህ አደጋዎች የ1 ሺህ 358 ሰዎች ህይወት ማለፉንና 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

የደረሰው አደጋ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም አሳሳቢነቱ  አሁንም መቀጠሉን ነው የተናገሩት፡፡ 


 

እንደ አገር የተቀናጀ የትራፊክ አደጋ መመዝገቢያ የመረጃ ቋት አለመኖሩ በችግሩ ልክ ምላሽ ለመስጠት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

የዛሬው ስምምነት ይህንን ችግር ሙሉ ለሙሉ የሚቀርፍ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

መረጃዎችን ለማሰባሰብ ጥቅም ላይ የሚውለው መተግበሪያ ""አር-ኤ-ዲ-ኤም-ኤስ" እንደሚባል የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በየትኛውም ቦታና ጊዜ የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን በአንድ ቋት በመያዝ ለፖሊሲ  ማሻሻያ ግብዓት ወይም ሌሎች እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አባሶ በበኩላቸው አገልግሎቱ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናወን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ከሪፎርም ስራዎቹ መካከል የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝ ስርዓትን ማዘመን አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱን የመንገድ ትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝ ለማዘመን እና ታማኝነት ያለው አሠራር ለመዘርጋት በተጠናው ጥናት መሰረት ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጋር በጋራ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ከክልል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የትራፊክ አደጋዎችን በመቀነስ ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኑን ጨምረው ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም