ቀጥታ፡

በሀዌላ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት አለፈ

ሀዋሳ፣ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል በሀዌላ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በአምስት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ክፍል ዳይሬክተር ኮማንደር ከበደ ኬኔራ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ አደጋው የተከሰተው ከሀዋሳ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሀዌላ ወረዳ ልዩ ስሙ ዋርካ ሰፈር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው ።

አደጋው የተከሰተው ከቀኑ በግምት  9:30 አካባቢ ከሀዋሳ ወደ ይርጋለም አቅጣጫ ተከታትለው የሚሄዱ ሶስት ተሽከርካሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሲሆን በአደጋውም የአራት ሰዎች ህይወት ሲጠፋ በአምስት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።

አደጋው የደረሰው የጭነት አይሱዙ ኮድ 3 የሰሌዳ ቁጥሩ 32804 አ.አ የሆነ በተለምዶ ዶልፊን እየተባለ የሚጠራ ተሽከርካሪ ከኮድ 3 የሰሌዳ ቁጥር 52430 ኦሮ እና ኤፍ ኤስ አር ኮድ 3 የሰሌዳ ቁጥር 00999 ሲዳ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ጋር በመከታተል ሲሄዱ በተፈጠረ ግጭት መሆኑን ተናግረዋል።

አደጋው እጅግ አስከፊ መሆኑን ተናግረው በአደጋውም ሁለት ሰዎች ወዲያው ሲሞቱ ሁለቱ ደግሞ ለህክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ሪፌራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እያገኙ መሆኑን ገልጸው የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰውም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ኮማንደር ከበደ አክለዋል።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሚገኝ የገለጹት ኮማንደሩ አሽከርካሪዎች የአካባቢውን አየር ንብረትና መልክዓ ምድርን በመለየት በተፈቀደላቸው የፍጥነት ወሰን በጥንቃቄ ማሽከርከር እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም