ቀጥታ፡

በ10 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች በአጀንዳ ማሰባሰብ የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ በአብዛኛው ተጠናቋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡- በ10 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች በአጀንዳ ማሰባሰብ የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ በአብዛኛው መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ የምክክር ሂደቱ ያለበትን ሁኔታ በማስመልከት በተለይም ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኘው ማህበረሰብ በአጀንዳ ማሰባሰብ እንዲሳተፍ ኮሚሽኑ በስፋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ለዚህም ወረዳዎች ተሳታፊዎቻቸውን እንዲመርጡ የማድረግ ስራ ከጥቂት አካባቢዎች በስተቀር ከሞላ ጎደል ተጠናቋል ብለዋል።

ሀረሪ፣ ሲዳማ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አፋር እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ላይ የተሳታፊ ልየታ ቀደም ብሎ የተጠናቀቀ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተሳታፊ ልየታ ዘግይቶ በተጀመረባቸው የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎችም ከግማሽ በላይ በሚሆኑ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ መከናወኑን ጠቅሰው በሚቀጥለው ሳምንት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ብለዋል።

በሶማሌ ክልል በሁለት ዞኖች በሚገኙ 25 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ እስከ ቀጣይ ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልልም የተሳታፊዎች ልየታ እየተከናወነ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ በክልሉ ካሉ 350 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን መርጠው አጠናቀዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የጅማ ዞን፣ ኢሉባቦር ዞን፣ የወለጋ ዞኖች፣ የምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኘው ህብረተሰብ ተሳታፊዎቹን በመምረጥ ላይ ነው ብለዋል።

በቀጣይ በሻሸመኔ ክላስተር ያሉ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ እንደሚከናወን ጠቅሰው፤ በክልሉ የተሳታፊ ልየታ ስራ እስከ ሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ብለዋል።

በአጠቃላይ ከአማራና ትግራይ ክልሎች በስተቀር በአጀንዳ ማሰባሰብ የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ ከሞላ ጎደል ተጠናቋል ነው ያሉት።

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ ለመጀመር ከክልሉ መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም ተባባሪ አካላትን ከተለያዩ ወረዳዎች ለመለየት እየተሰራ ሲሆን ተባባሪ አካላትን የሚያሰለጥኑ መምህራን በክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በመመልመል የማሰልጠን ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በትግራይ ክልልም የሀገራዊ ምክክሩን ሂደቶች ለመጀመር ኮሚሽኑ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንና ከጊዜያዊ አስተረዳደሩ ጋር ለሂደቱ አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ዙሪያ ውይይቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በግጭት እየተሳተፉ ያሉ አካላት የትጥቅ እንቅስቃሴን አቁመው ሰላማዊ አማራጭን እንዲከተሉና በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም