ቀጥታ፡

ህዳሴ ግድብ ለፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ በር የከፈተና ''ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ'' የሚለውን እሳቤ በተግባር ያረጋገጠ ነው-የዘርፉ ተመራማሪ

አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ለፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ በር የከፈተና ''ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ'' የሚለውን እሳቤ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን  የ"ኮኔክት አፍሪካ " ሚዲያ መስራችና የፓንአፍሪካኒዝም ተመራማሪ ማህሌት አየለ ገለጹ።

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የፓን አፍሪካኒዝም ተመራማሪና ''ኮኔክት አፍሪካ'' የተሰኘ የሚዲያ ተቋም መስራችና ባለቤት ማህሌት አየለ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት በኔዘርላንድ ነው፡፡

የፓን አፍሪካኒዝም ተመራማሪዋ ማህሌት አየለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክታለች።

ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸው የልማት ስራዎች የቀጣናውን አገራት ታሳቢ ያደረጉ ስለመሆናቸው ታሪክን አጣቅሰው አብራርተዋል።

የአድዋ ድል፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ፣ አህጉራዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች መገለጫዎች ይህንኑ በተግባር የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያነቃነቀና አብሮነታቸውን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም አንስተዋል ።

በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋ የሰጠና ፊታቸውን ወደ አገራቸው እንዲያዞሩ ያደረገ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑንም እንዲሁ።

በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ ጫናዎች እንደነበሩ የገለጹት ተመራማሪዋ ጫናዎቹን ለመመከትና ምላሽ ለመስጠት የተደረገው ጥረት ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን አስመልክታ የተገበረችው የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን በተግባር ማረጋገጥ የተቻለበትና ለሌሎች አፍሪካ አገራት አርአያ የሆነችበት እንደነበረም ጠቅሰዋል።

በአገር ውስጥም ሆነ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ጥቅም ዙሪያ የሚያደርጉትን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድቡ ለዘላቂ የአገር እድገት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተከትሎ የተደረገው የጋራ ርብርብ በልዩነት ውስጥ አንድነትን ያጎላ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በየትኛውም ሁኔታና አመለካከት ውስጥ ያሉ፣ አገራቸውን የሚወዱና ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ዜጎች የግድቡ ግንባታ ፍጻሜውን እስኪያገኝ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነው የጠየቁት።

''ሕዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ አድዋ ነው'' ያሉት ተመራማሪዋ የአድዋ ድል የቅኝ አገዛዝን ለመጣል የተደረገ ትግል ሲሆን የህዳሴ ግድብም በእጅ አዙር የሚደረግ ቅኝ አገዛዝን ለማስቀረትና ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን ለማምጣት የሚደረግ ትግል መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ የነጻነት ተምሳሌት ተብላ እንድትጠራ ማስቻሉን ጠቅሰው የህዳሴ ግድብም የኢትዮጵያ ምልክትና አርማ የሚሆንበት እድል ተፈጥሯል ብለዋል።

በተጨማሪም በአድዋ ድል የታየው ጽናት፣ የይቻላል መንፈስና አንድነት በህዳሴ ግድብ ላይ መደገሙ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ላይ የማይደራደሩ መሆናቸውን የሚያጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።  

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 95 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ግንባታው የተጀመረበት 13ኛ ዓመት በተለያዩ መርኃ-ግብሮች ተከብሯል።

 

 

                     

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም