የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት በሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ጥረቱን እንደሚቀጥል አስታወቀ

889

አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት በሱዳን ያለው ግጭት በዘላቂነት እንዲቆምና ሰላም እንዲመጣ ጥረቱን እንደሚቀጥል አስታወቀ።

ምክር ቤቱ የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት በዓል እና ለአዲስ አባል ሀገራት የአቀባበል መርሃ ግብር አካሂዷል።

አቀባበል የተደረገላቸው አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ኮትዲቯር፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብጽ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋምቢያ፣ ሴራሊዮን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው።

የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲኦዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ምክር ቤቱ በአህጉሪቱ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን ባደረገው ጥረት ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ለማቆምና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት የምክር ቤቱ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ ማዕቀፍ የመፍታት ሂደት ዐቢይ ማሳያ ነው ብለዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በሱዳን የተከሰተውን ግጭት በማቆም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ጥረት እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

ለዚህም ከአፍርካ ህብረት፣ ከኢጋድና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሆን ተፋላሚ ሃይላትን የማነጋገርና ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በቅርቡ በሚካሄደው የምክር ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ስብሰባ የሱዳን ጉዳይ በልዩ ትኩረት ምክክር እንደሚደረግበት ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ግጭቶችን የመፍታትና እንዳይከሰቱ የመከላከል ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የአፍሪካ ህብረት ለሰላምና ጸጥታ ምክር ቤቱ  ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት በቀይ ባህር አካባቢ የሚስተዋሉ ግጭቶች በምስራቅና ሰሜን  የሚገኙ አባል አገራት ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ በመረዳት ከሚመለከታቸው ጋር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ግጭትን አስቀድሞ መከላከል፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚያስችል አቅምና ትብበር ማጠናከር፣ የዴሞክራሲ ባህልን ማሳደግ ምክር ቤቱ ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት እንደሆኑ አንስተዋል።

የአፍሪካ ህብረት እ.አ.አ  ሐምሌ 9/2002 በደቡብ አፍሪካ ደርባን ባካሄደው የመጀመሪያ ጉባኤ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ፕሮቶኮልን ማጽደቁ ይታወቃል።

ፕሮቶኮሉ ከታህሳስ 2003 ጀምሮ በከፊል  ሲተገበር ቆይቶ ከ2004 የመጀመሪያዎቹ ወራት አንስቶ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ገብቷል።

የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት እኩል ድምጽ ያላቸው 15 አባል አገራትን የያዘ ሲሆን በአህጉሪቱ ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ የሚሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም