ቀጥታ፡

አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የማህበረሰብ ተወካዮች የሚያቀርቡት አጀንዳ ወሳኝ ነው-ኮሚሽኑ

ጅማ ፤ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡-  አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የማህበረሰብ ተወካዮች የሚያቀርቡት አጀንዳ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ  ምክክር ኮሚሽን  ገለጸ። 

ኮሚሽኑ ዛሬ በጅማ ከተማ  የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የማህበረሰብ ተወካዮችን እያስመረጠ ነው።


 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤  የአለመግባባት መንስኤዎችን ለመለየት ከተወካዮች የሚሰበሰብ አጀንጃ ወሳኝ ነው።

ለምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎች የሚሰበሰቡት ከማህበረሰቡ በመሆኑ የማህበረሰቡን ተወካዮችን ለማስመረጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር ውስጥ በምክክሩ ላይ ተሳታፊዎችን መለየትና ከተለዩ ተሳታፊዎች ደግሞ አጀንዳዎችን መሰብሰብና ለምክክር ማቅረብ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

የማህበረሰቡ ተወካዮች ሲመረጡ ነጻና ገለልተኛ በሆነ አግባብ መሆን እንዳለበት አመልክተው፣ተወካዮችም  መሰረታዊ የሆኑና የማህበረሰባቸውን ጥያቄዎች የሚያቀርቡ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

አገራዊ ምክክሩ ሁሉን አሳታፊና አካታች እንዲሆን እየተሰራ ነው ያሉት ዶክተር አምባዬ፣ይህም  ያጋጠሙትን ችግሮችን በሚፈታና  በአሳታፊነት መርህ የሚከናወን ነው ብለዋል።

ከሆሮ ጉዱሩ ዞን የመጣችው ወጣት ሌሊሴ ታደሰ በሰጠችው አስተያየት፤  ኮሚሽኑ የማህበረሰብ ተወካዮችን አቀራርቦ ለማነጋገርና ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብላለች። 

ይህም ሁሉንም የማህረሰብ ክፍሎች ያሳተፈና ጅማሮውም መልካም መሆኑን ተናግራለች።

ሌላው ተሳታፊ አቶ አበራ ጋዲሳ፤ የአገርን ሰላም ለማስከበርና በአንድነት ለመኖር የሚያስችል ምክክር ይደረጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በተለይም የህብረተሰቡን ሀሳብ አሰባስበው በምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮችን እየመረጡ መሆኑን የገለጹት ተሳታፊው፣ይህም ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያስችለናል ብለዋል።

በጅማ ከተማ ቀደም ሲል በተጀመረውና ሆሮ ጉድሩን ጨምሮ ከ7 ዞኖች የተውጣጡ 114 ወረዳዎችን ያሳተፈው የህብረተሰብ ተወካዮች የመረጣ መርሀ ግብር  ነገ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም