ቀጥታ፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም መጠናከር ሚናው የጎላ ነው-ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡- የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም መጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑን የአባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ተናገሩ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአድዋ ጦርነት በመቀጠል የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነትና ትብብር  የታየበት ሁሉም ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በላባቸውና በገንዘባቸው እየገነቡት የሚገኝ የታሪክ ማህደር ነው፡፡

የዚህ ዘመን ትውልድም ይህንን ወርቃማ አጋጣሚ በመጠቀም የራሱን ታሪክ ለመፃፍ ከዳር እስከ ዳር በአንድ ሐሳብ በመቆም ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ያለልዩነት ለአንድ ዓላማ በጋራ በመቆም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን ለማድረግ አሁንም ካሉበት ሆነው በቅርበት እየደገፉ ይገኛሉ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ከተጀመረ እነሆ 13 አመታትን አስቆጥሯል፡፡

ኢዜአ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቀጠናውን አገራት ሁለንተናዊ ትስስር ከማጠናከር አኳያ ምን አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲል የአባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪ ከሆኑት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ውሃ አጠርና የመሬት አቀማመጣቸው ለግድብ ግንባታ የማይመች መሆኑን ዶክተር ያዕቆብ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትሰራቸው የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድቦች አገራቱ የሃይል ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ ሁነኛ አማራጭ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀጣናውን በኢኮኖሚ ከማስተሳሰር ባሻገር የአካባቢው አገራት ዘላቂ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ በትብብር እንዲሰሩ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡  

ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ከቻለች አፍሪካንና መካከለኛው ምስራቅን በሃይል ማስተሳሰር እንደምትችል ተናግረዋል፡፡

የበለጸጉ አገራት በአብዛኛው ለኃይል ምንጭነት የሚጠቀሙት የኒኩለር ኃይል በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምታመነጨው ታዳሽ ኃይል ከአየር ንብረት ብክለት የጸዳ በመሆኑ በቀጣይ የበርካታ አገራት የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ማዕከል እንደምትሆን ምንም ጥርጥር የለውም ነው ያሉት፡፡

ይህን ፍላጎት ለማሟላት ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በላይ ለጋራ ልማት በጋራ መረባረብ ይገባናል ብለዋል፡፡

ባለፉት አራት ተከታታይ አመታት የግድቡን ውሃ ሙሌቱ በስኬት በማከናወን በአሁኑ ወቅት ግድቡ ከ 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ መያዝ ችሏል፡፡ 

አሁን ላይ ከኃይል ማመንጫው ሁለት ተርባይኖች ብቻ 750 ሜጋ ዋት በማመንጨት ኢትዮጵያውያንን የልማቱ ተቋዳሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

የግድቡ ግንባታ ባለፉት አስራ ሶስት አመታት በርካታ ውጣ ውረዶችን በማለፍ አሁን ላይ 95 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱ በቅርቡ መገለጹ ይታወሳል፡፡

 

 

 

 

   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም