ኖርዌይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለመጠቀም የምታካሂደው እንቅስቃሴ በዘርፉ ፈርቀዳጅ ሀገር ሊያደርጋት ይችላል ተባለ

273

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡- ኖርዌይ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ረገድ የምታከናውነው ተግባር ተሽከርካሪዎቹን በስፋት በመጠቀም ቀዳሚዋ ሀገር ሊያደርጋት እንደሚችል ተገለጸ።

ኖርዌይ ከአውሮፓውያኑ 2025 ጀምሮ የናፍጣና የቤንዚን ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ ክልከላ ማድረጓ ተዘግቧል።

የሃገሪቱ ዜጎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እንዲጠቀሙ ከፍ ያሉ ማበረታቻዎች እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ነው የተዘገበው።


 

የነዳጅ ተሽከርካሪዎች በሃገሪቱ ላይ ከፍ ያለ የአካባቢና የአየር ብክለት ማስከተላቸው ለዚህ ውሳኔ ገፊ ምክንያት መሆኑን የገለጸው የኖርዌይ መንግስት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት በዜጎች እንዲዘወተሩ ለማድረግም ከፍተኛ የተባለ የግብር ቅነሳ አድርጓል።

የግብር ቅነሳና መሰል ማበረታቻዎች ትርጉም ያለው ለውጥ በማምጣታቸው በሃገሪቱ ጥቅም ላይ ከዋሉት ተሽከርካሪዎች አብዛኞቹ የኤሌክትሪክ ሆነዋል ሲል ዘኢንዲፔንደት ዝግቧል።

በሀገሪቱ የሚገኙትን የናፍጣና የቤንዚን ተሽከርካሪዎች ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ ተክቶ ለማጠናቀቅ ጥቂት አመታት መውሰዱ እንደማይቀር በዘገባው ተመልክቷል። 

የመንግስት ቁርጠኝነት በዚሁ ከቀጠለ ሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች ሙሉ ሙሉ በኤሌክትሪክ የሚተኩ መሆኑን ነው ዘገባው ያተተው።

በኖርዌይ የልሂቃን ቡድን የመጓጓዣ ዘርፍ ተመራማሪ ኢንግቪልር ሮርሆልት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ ከ92 በመቶ በላይ ማደጉን አስረድተዋል።


 

ኖርዌይ የወሰደችው አይነት እርምጃ በሌሎች ሃገራት መተግበር ቢችል አሁን ያለው የነዳጅ ዋጋ ሊረጋጋ ከመቻሉም በላይ የአየርና የአካባቢ ብክለትም ሊቀንስ እንደሚችል ተመልክቷል።

ባሳለፍነው የአውሮፓውያን አመት በሃገሪቱ 1 መቶ 5 ሺህ የኤሌክትሪክ እና 76 ሺህ የነዳጅ  ተሽከርካሪዎች ተሽጠዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም