ቀጥታ፡

ለውጡ የዳር ተመልካችነትን አስቀርቶ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ አድርጎናል - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ለውጡ የዳር ተመልካችነትን አስቀርቶ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ አድርጎናል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ኢዜአ ከሐረሪ ክልል ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የመደመር ጉዞ የፓናል ውይይት ‘የለውጡ ትሩፋቶችና መደመር’ በሚል መሪ ሃሳብ በሐረር ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያ ብልፅግና ስኬት መዳረሻ በመሆኑ የዕለት ተዕለት የተግባር መመሪያ ማድረግ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

የመደመር እሳቤ የአብሮነት፣ የሰላም፣ የልማትና ብልፅግና እሴቶችን የሰነቀ መሆኑን ጠቅሰው በዚሁ አካሄድ ሁለንተናዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በተለይም በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ዲፕሎሚሲ መስክ የሚጠቀሱ ስኬቶች መገኘታቸውን ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት አጋር የሚለውን እሳቤ በማስቀረት ሁሉንም አሳታፊ ማድረግ ያስቻለ መሆኑንም ነው ርእሰ መስተዳድሩ ያብራሩት።

አጠቃላይ ሀገራዊ ለውጡ ሁሉንም ክልሎች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ ያደረገ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ትክክለኛ የፌዴራሊዝም ስርአት እውን እንዲሆን ያደረገ ትክክለኛ ለውጥ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከአገራዊ ለውጡ በፊት አገሪቱ ከፍተኛ እዳ ውስጥ እንደነበረች ገልጸው ይህንን የማቃለል ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዲፕሎማሲ አኳያ ትብብርና ትስስርን መርህ ያደረገና ለዜጎች ክብር የሚሰጥ በማድረግ ብዙ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

በአገራዊ ለውጡ በተደረገ ሪፎርም በርካታ ተቋማት አሁን ላይ የተሻለ ቁመና ላይ ይገኛሉ ሲሉም ተናግረዋል።

የሰላም ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁላችንም የጋራ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በቀጣይም የለውጡን ሂደት ጠብቆ በማስቀጠል የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በጋራ እንትጋ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም