አየር መንገዱ በአገር ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለማጠናከር መሰረተ ልማቶችን እያስፋፋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ በአገር ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለማጠናከር መሰረተ ልማቶችን እያስፋፋ ነው
ጂንካ ፤መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገር ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ለማጠናከር መሰረተ ልማቶችን እያስፋፋ እንደሚገኝ አስታወቀ።
አየር መንገዱ በጂንካ ኤርፖርት በስምንት ሚሊዮን ዩሮ ያስገነባውን የመንገደኞች ማስተናገጃ /ተርሚናል/ ዛሬ አስመርቋል ።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ ከውጭ አገራት በረራዎች ባሻገር በአገር ውስጥ ተደራሽ በመሆን ቱሪዝምና የኢንቨስትመንትን ዘርፉን ለማነቃቃት ትኩረት ሰጥቷል።
አየር መንገዱ የአገሪቷን ህዝቦች ሁለንተናዊ ትስስር ለማጠናከር ደረጃቸውን የጠበቁ የአየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን በክልል ከተሞች በመዘርጋት የበረራ አገልግሎቱን ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በጂንካ ኤርፖርት በስምንት ሚሊዮን ዩሮ የተገነባው የመንገደኞች ማስተናገጃ/ተርሚናል/ የአገር ውስጥ በረራዎችን ለማዘመን አየር መንገዱ ከሚያከናውናቸው የማሻሻያ ስራዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አየር መንገዱ በ22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በሚዛን ቴፒ አማን፣ ነገሌ ቦረና፣ ያቤሎ፣ ጎሬ መቱና ደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ግንባታ ለተሻለ አገልግሎትእያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽንና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።