የኮሪደር ልማቱ ቅርሶችን ሳይነካ በጥንቃቄ እየተከናወነ ነው- የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማቱ ቅርሶችን ሳይነካ በጥንቃቄ እየተከናወነ ነው- የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ቅርሶችን ሳይነካ በጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የኢትዮጵያን ሃብትና ቅርሶች በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በመጠገን ለትውልድ እንዲተላለፉ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በመዲናዋ የቆዩ አካባቢዎችና ቤቶች ሁሉ ቅርስ እንደማይሆኑ ጠቅሰው የአዲስ አበባን ኪነ-ሕንፃና ቀደምትነት የሚያሳዩ ደግሞ እየታደሱና እየተጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል።
አንድ ህንጻ ረጅም ዕድሜ ስላሰቆጠረ ብቻ ቅርስ ሊባል ስለማይችል ሊያሟላቸው የሚገባቸው መስፈርቶች መኖራቸውንም ዘርዝረዋል።
ለቅርስነት የስነ ህንጻው አሰራር ዘይቤ (ስታይል)፣ አገነባቡ፣ ውስጣዊና ውጫዊ ገጽታው እንዲሁም ዲዛይኑንና ሌሎችንም ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በመሆኑም የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በከተማ አስተዳደሩና በባለስልጣኑ ቅንጅት ቅርሶችን ሳይነካ በጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በመልሶ ግንባታና ኮሪደር ልማት ቅርሶች ተለይተውና ተመዝግበው እንዲጠበቁ እየተደረገ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ገልጸዋል።
የልማትና ቅርስ ጥበቃ ስራ ሚዛኑን ጠብቆ ማከናወን የተለመደ መሆኑን ጠቅሰው የቅርስ ጥበቃና ልማትን ማጣጣም ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።