ቀጥታ፡

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማነቃቃት የተከናወኑ የለውጥ ስራዎች በዘርፉ የተሻለ እድገት እንዲመዘገብ አድርገዋል - አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2016(ኢዜአ)፡- ባለፉት አምስት ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማነቃቃት የተከናወኑ የለውጥ ስራዎች በዘርፉ የተሻለ እድገት እንዲመዘገብ ማድረጋቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፤ የኮቪድ-19፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና የመካከለኛው ምስራቅ አለመረጋጋት እንዲሁም በሀገር ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች የኢንዱስትሪ አቅርቦት ሰንሰለቱን በማዛባት ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ገልጸዋል። 

በዚህ መነሻነትም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ለአምራች ዘርፉ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን መፍትሔ ለመስጠት ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል።


 

ለአብነትም የኢንዱስትሪ ዘርፍ የማምረት አቅም ከነበረበት 47 በመቶ ወደ 56 በመቶ  እንዲሁም የገበያ ድርሻውን ከነበረበት 30 ከመቶ ወደ 39 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ፣ የሰው ሃይልና የሃይል አቅርቦት አቅም ያላት  በመሆኗ አምራች ኢንዱስትሪውን የማጠናከር ስራ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታትም አምራች ኢንዱስትሪው ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችን በመቋቋም ያስመዘገበው ስኬት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት አይተኬ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ የንግድ ሚዛን የተጣጣመ አይደለም ያሉት አቶ መላኩ፤ በዚህም 96 የምርት አይነቶችን በመለየት የገቢ ምርቶችን ለመተካት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ገቢ ምርቶችን ለመተካት በተከናወነ ተግባር ከ1 ቢሊየን አሜሪካን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው ምርቶችን በመተካት ትርጉም ያለው ስራ መሰራቱን አንስተዋል። 

ለተኪ ምርት ልማት የተሰጠው ትኩረትም በንግድ ትስስር፣ ስራ ዕድል ፈጠራ፣ ጥሬ ዕቃ አጠቃቀም፣ ለውጭ ምንዛሬ ዕድገትና ለንግድ ሚዛን መጠበቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በርካታ ፋብሪካዎች ወደስራ እንዲመለሱና አዳዲስ ፋብሪካዎችም እንዲከፈቱ በማድረግ በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ዕድገትና መነቃቃት መፍጠሩን አስረድተዋል።

ንቅናቄውም አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ፣ የመሰረተ ልማት፣ የመስሪያ ቦታ አቅርቦትና የግብዓት ትስስር ችግር መፍትሔ እንደሚያስገኝም ተናግረዋል።

በቅርቡም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የድጋፍ ቡድን በክልሎች ያደረገው ምልከታ ግብረ መልስ ንቅናቄው ለአምራች ኢንዱስትሪው መነቃቃት ጉልህ ፋይዳ ያበረከተ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ከፍተኛ፣ መካከለኛና አነስተኛ አምራች ኢንተርፕራይዝ የምርታማነት አቅም ለማሳደግ ተጨማሪ ድጋፍ በመስጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግስት ተቋማት የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርቶችን እንዲጠቀሙ ያስቀመጡት አቅጣጫ በገንዘብ ሚኒስቴር መመሪያ ተደግፎ ተግባራዊ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህም መንግስት ለሀገር ውስጥ ተኪ ምርት ልማት ትኩረት መስጠቱን የሚያሳይ በመሆኑ የገበያ ድርሻን በማሳደግ አምራች ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት አዎንታዊ ሚና እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም