በአስተዳደሩ የውሃ ተቋማት በመጠገን 90 ሺህ ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል 

ሰቆጣ ፤ መጋቢት 25 /2016 (ኢዜአ)፡- በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የውሃ ተቋማትን በመጠገን ከ90 ሺህ በላይ ህዝብ መልሶ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን የአስተዳደሩ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።  

የመምሪያው የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ጥናት ዲዛይን ባለሙያ አቶ ታደሰ አዳነ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ 194 የውሀ ተቋማቱ ተጠግነው ለአገልግሎት የበቁት ባለፉት ስምንት ወራት ነው።

አነስተኛ ፣መለስተኛ ጥልቅ ጉድጓድና የእጅ ቧንቧዎች ተጠግነው ለአገልግሎት በመብቃታቸው 90 ሺህ ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።


 

በውሃ ተቋማት ጥገና በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች 21 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ገልፀዋል። 

ድርቅ በተከሰተባቸው በሰሃላ ወረዳ በሚገኙ ሰባት ቀበሌዎች የሚስተዋለውን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ በክልሉና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የውሃ ቦቲዎችን ለመላክ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል። 

በሰቆጣ ዙሪያ የ01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሳሙኤል በሬ እንዳሉት፤ በአካባቢያቸው የንፁህ መጠጥ የሚያገኙበት ቧንቧ በመበላሸቱ ለሰባት ወራት ተቸግረው ቆይተዋል። 

በአሁኑ ወቅት ቧንቧ ተጠግኖ ለአገልግሎት በመብቃቱ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸውና ችግራቸው መፈታቱን ተናግረዋል። 

አቶ ሞገስ ሃይሌ በበኩላቸው፤ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት መጠገን በመቻሉ የእናቶችን እንግልትና ስቃይ አስቀርቷል። 

በብሄረሰብ አስተዳደሩ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋኑ 59 በመቶ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም