ቀጥታ፡

የለውጡ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎለብትና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ለማድረግ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ሶዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር ራሄል ባፌ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን እንደመጡ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጋቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የተለያየ ሀሳብ ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰላማዊ ትግል በማድረግ በህዝብ ይሁንታ ስልጣን መያዝና አገርና ህዝብ ማገልገል እንዲችሉ የመጫወቻ ሜዳውን ማመቻቸታቸው የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት መልካም ጅማሮ መሆኑን አንስተዋል።

የለውጡ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የጀመራቸው ስራዎች በዚያው ፍጥነት እንዲቀጥሉ በማድረግ ረገድ ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ መንግስት ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በተለይ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ተሳታፊ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው፥ የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለማጠናከር የነበረው ተነሳሽነትና እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በመንግስት ኃላፊነት ተሾመው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ማድረጉ በህዝብና በመንግስት መካከል መተማመን እንዲፈጠር በጋራ ለሀገር ልማት መስራት የሚያስችል በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል ነው ያሉት።

ነገር ግን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ የነበሩ መልካም ጥረቶች በሚፈለገው ልክ መቀጠል እንዳልቻሉም አንስተዋል።

በተለይ መንግስት በሚያከናውናቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያሳተፈ ቢሆን የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆንም ነው የተናገሩት።

ገዥው ፓርቲ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ ምህዳር ለመፍጠር የጀመራቸውን ስራዎች የበለጠ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አዲሱ አረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ካከናወናቸው ተግባራት ግንባር ቀደሙ የፖለቲካ ምህዳሩ ላይ የነበሩ መሰረታዊ ችግሮችን መፍታት ነው ብለዋል።

በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ እስር ቤት የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ማህበራዊ አንቂዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ነጻ እንዲሆኑ መደረጉን አንስተዋል።

በውጭና በአገር ውስጥ በትጥቅ ትግል ስልጣን የመያዝ ፍላጎት የነበራቸው ቡድኖች ወደ አገራቸው በመግባት በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋማት ከህግ ማሻሻያ ጀምሮ ነጻና ገለልተኛ እንዲሆኑ  በማድረግ ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን አስረድተዋል።

የተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት እንዳይሰሩ ሲያደርግ የነበረው የጸረ-ሽብር አዋጅ፣ የሚዲያና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የፍትህ ተቋማትን በተመለከተ የህግ  ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አንስተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበትና ሀሳባቸውን በነጻነት የሚያንሸራሽሩበት የጋራ ምክር ቤት በየደረጃው እንዲቋቋም መደረጉም ሌላው የለውጡ መንግስት ስኬታማ ስራ ነው ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የመንግስት ስልጣን በማካፈል አገራቸውን በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች እንዲያገለግሉ ማድረጉ በጋራ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም ገልጸዋል።

መንግስት ቀደም ሲል በአገሪቷ የነበሩ ቁርሾዎች በፍቅርና በእርቅ እንዲቋጩ ለማድረግ የሽግግር ፍትህ ፖለሲ እንዲወጣና አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አንዲቋቋም ማድረጉ የፖለቲካ ባህሉን ለማዳበርና ቸግሮችን በንግግር ለመፍታት ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

በለውጡ ዓመታት የተጀመሩ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋትና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎች በቀጣይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ አዲሱ ገልጸዋል።

የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲ በማደራጀቱ፣ ሀሳቡን በነጻነት በመግለጹ፣ መንግስትን በሰላማዊ መንገድ ተፎካክሮ ለማሸነፍ በመንቀሳቀሱ ተጠያቂ የሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራርም ሆነ አባል አለመኖሩንም ነው የገለጹት።

ይሁንና አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላት  ከጽንፈኛ ቡድኖች ጋር በመተባበር የአገርና የህዝብን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል እንደሚሞክሩ አንስተዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም