አዋጁ ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖርና የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ያለመ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር፣ ሕገ ወጥ የደላላ ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስና የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ያለመ መሆኑ ተገለጸ። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሦስተኛ ዓመት የስራ ዘመን 19ኛ መደበኛ ስብሰባው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን በሦስት ድምጸ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። 


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጂጌ አዋጁን በተመለከተ የድጋፍ ሞሽንና ማብራሪያ አቅርበዋል። 

አዋጁ ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር፣ ሕገ ወጥ የደላላ ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስና የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል። 

በአዲሱ አዋጅ መሰረት አከራይ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ የሚችለው ተቆጣጣሪው አካል የሚወስነውን ጭማሪ መሰረት በማድረግ  መሆኑም ተመላክቷል።

አዋጁ የአከራይ ተከራይ ውልን በተመለከተ፣ የተቆጣጣሪ አካል ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም ውል ማቋረጥን በተመለከተ ድንጋጌዎችን መያዙን ጠቅሰዋል። 

በአከራይና ተከራይ መካከል ሚዛናዊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖር እና ተከራይ የተረጋጋ ህይወት እንዲመራ ማድረግ የአዋጁ ዓላማ መሆኑን አብራርተዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) የአዋጁን ዝርዝር ያብራሩ ሲሆን፥ በአዋጁ መሰረት ተቆጣጣሪ አካል ውል የሚያዘጋጅ ሲሆን በውሉ መሰረት አከራይና ተከራይ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የውል ስምምነት ይፈራረማሉ ብለዋል። 

በውሉ መሰረት አንድ አከራይ አዲስ ቤት ለመከራየት ውል የሚገባን ተከራይ ከሁለት ወር በላይ ቅድመ ክፍያ መጠየቅ አይችልም ያሉት ሚኒስትሩ፥ ይህም በዜጎች ላይ የሚፈጠርን የኢኮኖሚ ጫና ለማቃለል ታስቦ የተዘጋጀ ስለመሆኑ አስረድተዋል። 

በአዋጁ መሰረት የተቆጣጣሪው አካል ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለቤት ኪራይ የሚደረግን የዋጋ ጭማሪ በየዓመቱ ሰኔ 1 ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፥ ጭማሪውም ከሰኔ 30 ጀምሮ ለአንድ ዓመት የሚጸና ይሆናል ነው ያሉት።

አከራይ በነባር ተከራይ ወይም አዲስ ተከራይ ላይ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ የሚችለው ተቆጣጣሪው አካል ነባራዊ ሁኔታውን እያየ የሚወስነውን ጭማሪ መሰረት በማድረግ ብቻ እንደሆነ በአዋጁ መደንገጉንም አንስተዋል።

አዲስ የመኖሪያ ቤት ሰርቶ ለኪራይ ያቀረበ አከራይ በዚህ አዋጅ መሰረት ከሚወጡ የቤት ኪራይ ዋጋ ጣሪያ ግዴታዎች የመጀመሪያውን የቤት ኪራይ ውል ካስመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ለሚቆጠር አራት አመት ነጻ ይሆናል።

አዋጁ የመኖሪያ ቤትን ሳያከራዩ በባዶ ወይም በሌላ አግባብ ለንግድ ወይም ለመኖርያ ወይም መሰል ተመጣጣኝ ማህበራዊ ፋይዳ ያለው አግልግሎት ሳይሰጥ ከአንድ ዓመት በላይ የሚያቆዩ የቤት ባለቤቶች የቤቱ የንብረት ግብር ተመን 25% የሚያክል ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ አሰራር ከፍተኛ የቤት እጥረት ባለባቸው የከተማ አስተዳደሮች በመመሪያ ሊዘረጋ እንደሚችል አብራርተዋል።
 
ዶክተር ጌዲዮን እንዳሉት አዋጁ በክልል ዋና ዋና ከተሞች የሚተገበር ሲሆን እንዳስፈላጊነቱ ነባራዊ ሁኔታውን እያዩ ክልሎች ተጨማሪ ከተሞች ላይ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ በአዋጁ ድንጋጌ መሰረት ተፈቅዷል።
 
አንድ አከራይ በአስገዳጅ ሁኔታ በባንክ ዕዳና እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ቤቱን ለመሸጥ ቢገድድ ተከራይ ቤት መፈለጊያ 6 ወር ጊዜ ሊሰጠው እንደሚገባም አዋጁ መደንገጉን አስረድተዋል።

ተከራይ በውሉ ላይ የተቀመጡትን ግዴታዎች እስካሟላ ድረስ ውሉ እስከሚጠናቀቅበት ሁለት ዓመት ድረስ የመቆየት መብት እንዳለውም አመልክተዋል። 

ይሁን እንጂ ተከራይ የተከራየው ቤት ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ፣ የአካባቢ ሰላምና ጸጥታ ካወከ በውሉ ከተቀመጠው ውጭ ህገ ወጥ ተግባር ከፈጸመ አከራይ ያለማስጠንቀቂያ ከቤቱ ማስለቀቅ እንደሚችል መደንገጉንም ገልጸዋል። 

በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙ የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ፣ ሆቴል፣ ሪዞርት፣ የእንግዳ ማረፊያና ሌሎች በንግድ ፈቃድ መሰረት በሚከራዩ ቤቶች ላይ አዋጁ ተፈጻሚ እንደማይሆን ገልጸዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው አዋጁን ለማዘጋጀት የሌሎች አገራት ተሞክሮ ከመቀሰሙም ባለፈ የችግሩን ስፋት ለመረዳት ጥልቅ ጥናት መደረጉን ተናግረዋል።

የተከራይ መብቶችን ማስጠበቅ እንዲሁም አከራይ ደግሞ ሕጋዊነትን ተላብሶ እንዲሰሩ ማድረግ ሌላው ዓላማ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ተከራይ ለቤት ኪራይ የሚያወጣው ክፍያ ከ30 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ መኖሩን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ በኢትዮጵያ ለቤት ኪራይ ከ70 በመቶ በላይ እየወጣ መሆኑ የጉዳዩን አሳሳቢነት እንደሚሳይ አመልክተዋል። 

አዋጁ ለኑሮ ጫናው ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት መንግስት እየወሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች መካከል መሆኑንም ተናግረዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም