ቀጥታ፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያና ዳግም የድል ታሪክ የተጻፈበት ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ፈተናዎችን በህብረ ብሔራዊ  አንድነት በመሻገር ተጨባጭ ውጤት ያሳዩበትና ዳግም ታሪክ የጻፉበት ፕሮጀክት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት 13ኛ ዓመት "በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተከብሯል።


 

በመርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ሀብታቸውን በራሳቸው አቅም የማልማት መብታቸውን በተግባር ያረጋገጡበት ነው፡፡

አክሱም ሐውልትን፣ ላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ ፋሲል ግንብን፣ ጀጎልንና የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግስት የታነጹት በኢትዮጵያውያን ሐብትና ጥበብ  መሆኑን አውስተው፥ የህዳሴ ግድብም በዚህ ዘመን ትውልድ እውን የሆነ ግዙፍ የሀገር ሀብት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ግድቡ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባታው አሁን ላይ 95 ነጥብ 8  በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በተከታታይ የውሃ ሙሌቱን በማከናወን በአሁኑ ወቅት ከ42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ መያዙን ገልጸዋል፡፡

ታሪካዊ ጠላቶቻችን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ምክንያቶችን በመደርደር ሊያስቆሙን ቢሞክሩም እንዳሰቡት ግን አልሆነላቸውም ብለዋል።

ይህ የሆነው ህዝብ እና መንግስት በአንድነትና በትብብር መስራት በመቻላቸው መሆኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ግድቡ የኢትዮጵያውያን የዓድዋ ዘመን ህብረ ብሔራዊ አንድነት እና ድል ዳግም የታየበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አሁን የደረሰበት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ከተባበርን ተግዳሮትን በድል ተሻግረን ውጤት ማስመዝገብ እንደምንችል በተግባር የተማርንበት ነው ብለዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሐብታሙ ኢተፋ፥ በአራቱም አቅጣጫ የሚፈስሱ ወንዞች ያለማንም ከልካይ የኢትዮጵያን አፈር ጠራርገው ሲወስዱና ተፋሰሶችን ሲያራቁቱ መቆየታቸውን አውስተዋል።


 

ከዚህ በፊት ከውሃ ሀብት ሲመነጭ የነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል መጠን ከ4 ሺህ ሜጋ ዋት እንደማይበልጥ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ከአለን የውሃ ሐብት አንጻር ሲታይ 8 በመቶው ብቻ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ በተሰጠ አመራር ከህዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች ብቻ 750 ሜጋ ዋት በማመንጨት ህዝቡን የጥረቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ በበኩላቸው፥ እስካሁን ድረስ ለግድብ ግንባታ ከህዝቡ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።


 

የግድብ ግንባታ ቀሪ ስራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ህብረተሰቡ ከገንዘብ መዋጮ ባሻገር በተፈጥሮ ሃብት ልማት እና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም