በግብርናው መስክ ጠንክረን በመስራት ሀብት ለመፍጠር የጀመርነውን ጥረት እናጠናክራለን- ተሸላሚ ሞዴል አርሶ አደሮች

ሀዋሳ፤ መጋቢት 24/ 2016 (ኢዜአ)፡-  በግብርና ዘርፍ ጠንክረው በመስራት ሀብት ለመፍጠር የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በሲዳማ ክልል ተሸላሚ ሞዴል አርሶ አደሮች ገለጹ። 

በክልሉ በ2015/2016 የምርት ዘመን በእርሻ ልማት ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ 131 አርሶ አደሮች ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በተገኙበት ትናንት እውቅናና ሽልማት መሰጠቱ ይታወሳል።


 

በሲዳማ ክልል የመጀመሪያው የአርሶ አደሮች ፌስቲቫል ላይ የተሸለሙ አንዳንድ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንዳሉት፣ መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ ጠንክረው በመስራት ሀብትና ንብረት አፍርተው ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከአርሶ አደሮቹ መካከል የደራ ኦቲልቾ ወረዳ ሞዴል አርሶ አደር መለሰ ቱንሲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ሁሉም በሥራው ጠንክሮ መስራት ከቻለ ውጤታማ መሆንና ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል።

በተሰማሩበት የግብርና ልማት ከግብርና ቴክኖሎጂዎች በተጨማሪ የቤተሰቦቻቸውን ጉልበት አሰባስበው ጠንክረው በመስራታቸው ለውጤት እንደበቁ ገልጸዋል።

በሰፊ መሬት ላይ እያለሙት ካለው ቡና በተጨማሪ አትክልት፣ ፍራፍሬና ሰብል በቋሚነት በማልማት ሀብት ማፍራት መቻላቸውንም ተናግረዋል።

ሽልማቱ ሥራቸውን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዳነሳሳቸው ገልጸው፣ በቀጣይም ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ ተናግረዋል።

"የገቢ አማራጬን ለማስፋት በወረዳው የቡና መፈልፈያ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ዕቅድ አለኝ" ያሉት አርሶ አደሩ አደር መለሰ፣ ለዚህም ሁለት ሄክታር መሬት ጠይቀው ከወረዳው አስተዳደር ምላሽ እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ሌላው እውቅናና ሽልማት የተበረከተላቸው ሞዴል አርሶ አደር አስፋው ዘርፉ በበኩላቸው፣ በግብርና ልማቱ ጠንክረው በመስራታቸው ዓመታዊ ገቢያቸው ከ500ሺህ ብር በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

በገበያ ተፈላጊ ለሆኑ ምርቶች ትኩረት መስጠታቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ፤ አምርተው ለገበያ ካቀረቧቸው ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ድንችና የተለያዩ ፍራፍሬዎች ባገኙት ገቢ ኑሯቸው እየተለወጠ መምጣቱን ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ ከግብርና ሥራቸው በተጨማሪ በሌላ መስክ ለመሰማራት ማቀዳቸውን ጠቁመው፣ የክልሉ መንግስት ለሥራቸው እውቅና ሰጥቶ መሸለሙ ብርታት እንደሰጣቸው ገልጸዋል።

በግብርናው ልማት ስኬታማ መሆናቸው ታይቶ ለአትክልትና ፍራፍሬ ምርታቸው መሸጫ ቦታ በማግኘታቸውም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ አርሶ አደሩን ለዓመታት ሲሰራበት ከነበረው ልማዳዊ የግብርና አስራር ለማስወጣት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በእዚህም ከቤት ፍጆታ ባለፈ የተሻለ ገቢ የሚያስገኝለትን ምርት እንዲያመርት አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገለት ይገኛል ብለዋል።

በዚህም የክልሉ አርሶ አደር በዓለም ገበያ ጭምር ተፈላጊ የሆኑ ቡናና ሌሎች ምርቶችን የማምረት ልምዱ በየጊዜው እያደገና ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን ነው ያስረዱት።

"በቀጣይም ሞዴል አርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂና የተሻሻሉ አሰራሮችን በተሻለ ሁኔታ በመተግበር ሀብት ለማፍራት የጀመሩትን ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሰራል" ብለዋል።

በተለይ ሞዴል አርሶ አደሮች ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በምርታማነት ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ በክልሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ተጠቃሚ የሆኑ 800ሺህ አርሶ አደሮች በግብርናው መስክ ስኬታማ እንዲሆኑ ቢሮው የክህሎት ስልጠና፣ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ያቀርባል ብለዋል።

በእዚህም በክልሉ ፈጣን የግብርና እድገት እንዲመጣ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አቶ መምሩ ያስታወቁት።

ትናንት በተካሄደው የሲዳማ ክልል የመጀመሪያው የአርሶ አደሮች ፌስቲቫል ላይ ሞዴል አርሶ አደሮች እንዳስመዘገቡት ውጤት የውሃ መሳቢያ ሞተር፣ ሜዳሊያ እና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም