የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለኢንተርፕራይዞች ልማት የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለኢንተርፕራይዞች ልማት የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለኢንተርፕራይዞች ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
በኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የተመራ የዓለም ባንክና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ የካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ ብድር ተጠቃሚ የሆኑ ኢንተርፕራይዞችን ጎብኝተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ፤ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በሚያገኙት ብድር በኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።
በዓለም ባንክ ድጋፍ ኢንተርፕራይዞችን የመለየትና የማሰልጠን ሥራ በማከናወን መንግሥት የመሥሪያ ቦታና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም የብድር ድጋፍ አገልግሎቱም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም የመሥሪያ ካፒታልና ማሽነሪ ድጋፍ በማቅረብ እገዛ ማድረጉንም ነው የገለጹት።
በቀጣይም የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ለኢንተርፕራይዝ ልማት ለሰጠችው ትኩረት ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዓለም ባንክ የሥነ-ምግባርና የውስጥ ፍትሕ አገልግሎቶች ቡድን ምክትል ፕሬዝዳንት ሊሳ ሮዘን፤ ኢንተርፕራይዞቹ ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ በሆኑ መስኮች መሰማራታቸውን አድንቀዋል።
በዚህ መነሻነትም የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር)፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢንተርፕራይዞችን የሚደግፍ የዓለም ባንክ የብድር ሥምምነት ፕሮጀክት ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ አማካኝነት ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተደረገው የብድር አገልግሎትም የመሥሪያ ካፒታልና የማሽነሪ ድጋፍ በማቅረብ ውጤታማ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተለይም በካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ ያለዋስትና የሚቀርበው የማምረቻ ማሽነሪ የኢንተርፕራይዞችን ምርታማነት በማሳደግና የዕውቀት ሽግግር እንዲፈጠርም ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል ነው ያሉት።
የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ ያደረገውን የፕሮጀክት ድጋፍ አፈጻጸም ምልከታ ማድረግ የሥራ ጉብኝቱ ዋና ዓላማ እንደሆነ ተገልጿል።
የሥራ ኃላፊዎቹም በአዲስ አበባ አያትና ቃሊቲ አካባቢ በሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑትን የኢቲኤም ጨርቃጨርቅና አሁን ኢንጂነሪንግ ኢንተርፕራይዞችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።