ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ማሪታይም የባህር ሃይል አባላትን አስመረቀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ማሪታይም ባቦጋያ አካዳሚ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል አባላትን አሠልጥኖ አስመረቀ፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ማሪታይም ባቦጋያ አካዳሚ ለኢትዮጵያ ባህር ሃይል አባላት ከመርከብ የሚነሳ እሳት እንዴት መከላከል እና የእሳት አደጋ ከተነሳም በፍጥነት መቆጣጠር የሚያስችል ስልጠና ሠጥቷል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች የሥራ መመሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ዋና አዛዥ ተወካይ ሬር አዲሚራል ናስር አባድጋ የባህር ሃይል ሠልጣኝ ተመራቂዎች የኢትዮጵያ ባህር ሃይል የጀርባ አጥንት በመሆናችሁ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ መወጣት አለባችሁ ብለዋል። 


 

አዛዡ አክለውም የባህር ሃይል አባል መሆንና መርከብ ላይ ግዳጅን መወጣት ጥሩ ሥነ-ምግባር፤ ወታደራዊ ዲሲፒሊን፤ ጠንካራ ግዳጅ አፈፃፀምና የህይወት መስዋዕትነትን ጭምር የሚጠይቅ ሙያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በመሆኑም ተመራቂ የመርከብ ሙያተኞች በስልጠና ያገኛችሁትን አቅም ወደ ተግባር በመለወጥ ሙያዊ ሃላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ 


 

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባቦጋያ አካዳሚ ዲን ቺፍ ቴድሮስ ሚሊዮን ተመራቂዎቹ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል አባላት በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር የተደገፈ ሥልጠና በአግባቡ መከታተላቸውን ገልፀዋል። 

አስተያየት ከሰጡ ተመራቂዎች መካከል መርከብ ላይ ስንወጣ በርካታ ውጣ ውረዶች የበዛበት በመሆኑ በመርከብ ላይ የሚነሳ የእሳት አደጋን በቀላሉ ለማጥፋት የሚያስችል ሙያዊ ስልጠና ወስደናል ሲሉ መግለጻቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም