በአማራ ክልል በተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም የተከናወነው ስራ የአርሶ አደሮች ኑሮ እንዲሻሻል አግዟል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም የተከናወነው ስራ የአርሶ አደሮች ኑሮ እንዲሻሻል አግዟል
ባህር ዳር ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም የተከናወነው ስራ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮች ኑሮ እንዲሻሻል ማገዙን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ማጠናቀቂያ ኮንፍረንስ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በፕሮግራሙ የሰባት ዓመት ቆይታ የአርሶ አደሩን ኑሮ የቀየሩ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም የመስኖ አውታሮችን በመገንባትና በተፋሰስ ልማት በተከናወኑ የግብርና ስራዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ አርሶ አደሮች ኑሮ እንዲሻሻል ማገዙን ተናግረዋል።
የተሻሻሉ አሰራሮችና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ከማገዝ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲጎለበት ማድረጉን ገልጸዋል።
በቀጣይም በፕሮግራሙ ሲሰራባቸው የነበሩ ተግባራትን ወደ መደበኛ የልማት ስራ በማስገባት ልማቱ በሌሎች አርሶ አደሮች ዘንድ እንዲሰፋና እንዲሰርፅ እንደሚደረግ ዶክተር ድረስ አመልክተዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የተሳትፏዊ ግብርናና አየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም ማናጀር አቶ በለጠ ጌታነህ በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ ባለፉት ሰባት ዓመታት በ21 ወረዳዎች የተለያዩ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከ6 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት የሚችሉ 35 አነስተኛ የመስኖ አውታሮችን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ከ12 ሺህ 600 የሚበልጡ አርሶ አደሮች የመስኖ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ በምግብ ዋስትና እራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቁመው፤ በተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንደተቻለ አመልክተዋል።
‘‘አነስተኛ የመስኖ አውታር መገንባቱ ሳልሰለች ሰርቼ ከድህነት እንድላቀቅ አድርጎኛል’’ ያሉት ደግሞ በሰሜን ወሎ ዞን ግዳን ወረዳ የ09 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ በላይነሽ መጋቢ ናቸው።
በተመቻቸላቸው የመስኖ አውታር በግማሽ ሄክታር መሬት ጤፍ፣ ስንዴና ሽንኩርት በማልማት ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ከምርት ሽያጭ በዓመት እስከ 190 ሺህ ብር ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ በለሳ ወረዳ የአርባያ ቀበሌ አርሶ አደር ጀጃው ሰፈፈ እንዳሉት፤ በፕሮግራሙ የተገነባው የመስኖ አውታር ሩብ ሄክታር መሬት በመስኖ አልምተው እንዲጠቀሙ አግዟቸዋል።
ከሚያመርቱት ምርት በምግብ እራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ምርት ለገበያ በማቅረብ በየዓመቱ ከ200 ሺህ ብር ያላነሰ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል።
በኮንፍረንሱ ላይ ከክልሉ ግብርና ቢሮ፣ ከምርምርና ከፕሮግራሙ የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል።