ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናው ሁለንተናዊ የጋራ ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናው ሁለንተናዊ የጋራ ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የዓለም አቀፍ የውኃ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ዶክተር አብዱልከሪም ሰይድ ተናገሩ። 

ዶክተር አብዱልከሪም ሰይድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ቀጣናውን ከሚያስተሳስሩ የተፈጥሮ ኃብቶች አንዱ የሆነውን የውኃ ኃብት በጋራ የተጠቃሚነት መርህ ግድብ መገንባቷ ለአብነት የሚወሰድ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ለሚፈተነው ምስራቅ አፍሪካ፤ የተፈጥሮ ኃብት በማልማት ለጋራ ልማት ማዋል እንደሚገባ ትምህርት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የሕዳሴ ግድብ በምስራቅ አፍሪካ ትብብርና ትስስር በማጠናከር ለቀጣናውና ብሎም ለአህጉሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ነው ያስረዱት።  

እንደ ዶክተር አብዱልከሪም ገለፃ፤ ሀገራት የምጣኔ ኃብት ትስስራቸው ሲጎለብት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስቀጠል የሚያስችል ሁለንተናዊ ትብብር ይጠናከራል። 

ከዚህ አንጻር የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ በዘለለ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋትም የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት።

ግድቡ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለመመለስ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረትም በመደገፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።  

ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በመገንባት ሂደት የሚነሱ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የነበሩ ጥረቶችም የሚበረታቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በግድቡ ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶች በሥምምነት እንደሚቋጩ እምነታቸውን ገልፀዋል።

ላለፉት 20 ዓመታት የምስራቅ አፍሪካ ቢሮውን በኢትዮጵያ ያደረገው የዓለም አቀፍ የውኃ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ የውኃ መረጃ፣ የውኃ አስተዳደር አቅምን በማሳደግ፣ በውኃ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ውይይቶችን በማመቻቸት እየሰራ ይገኛል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 95 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ግንባታው የተጀመረበት 13ኛ ዓመት በተለያዩ መርኃ-ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም