የትላንት፣ የዛሬና የነገ ገዥ ምዕራፎችን በማስተሳሰር ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብት የወል ትርክት መገንባት ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የትላንት፣ የዛሬና የነገ ገዥ ምዕራፎችን በማስተሳሰር ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብት የወል ትርክት መገንባት ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ የትላንት፣ የዛሬና የነገ ገዥ ምዕራፎችን በማስተሳሰር ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብት የወል ትርክት ለመገንባት በጋራ መሥራት ይገባል ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር ዴኤታ ካሊድ አልዋን ተናገሩ።
ኢዜአ ከሐረሪ ክልል ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የመደመር ጉዞ የፓናል ውይይት "የለውጡ ትሩፋቶችና መደመር" በሚል መሪ ሃሳብ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በፓናሉ ላይ "መደመርና የጋራ ትርክት ፋይዳ" በሚል የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ካሊድ አልዋል የኢትዮጵያ ትርክት መልኮችና መደመርን ከብሔራዊ ትርክት ማዕቀፍ አኳያ ተንትነዋል።
ትርክት ያለፈው ጉዞ፣ አሁናዊ ሁኔታና የነገ መዳረሻን የሕይወት መስመር አመላካች ፅንሰ-ሃሳብ፣ የዕይታ ማዕቀፍ ና ታሪክን እንደ እርሾ ወስዶ የነገን መዳረሻ የሚተልም መሆኑን ጠቁመዋል።
ትርክቶችን በአግባቡ መረዳት ትላንትን በአግባቡ ለመረዳት፣ የዛሬን አኗኗር ቅርጽ ለማስያዝ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፤ አዎንታዊና አሉታዊ ትርክቶችን በቅጡ ተንትኖ ለሀገር ግንባታ የሚበጀውን መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የአሉታዊ ትርክት ለብዙ እልቂት የሚዳርግ መሆኑን የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በማሳያነት ጠቅሰው፤ በአንጻሩ አዎንታዊ ትርክት የገነቡ ሀገራት ደግሞ በዓለም ላይ ኃያልና የበለፀጉ መሆን እንደቻሉ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የተራራቀ ትርክት እንዳለ ገልጸው፤ በአንድ በኩል ፍጹም አንድነት የሚያቀነቅን፣ ብዝኃነትን የካደና አንድነትን አንድ ዓይነት አድርጎ የሚወስድ እንደሆነ ገልፀዋል።
ይህ ዓይነቱ ትርክት የአፀፋ ትርክት እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸው፤ የተፈጠረው የአጸፋ ትርክት ደግሞ የብሔር ጽንፈኝነት የተጠናወተው፣ ጨቋኝና ተጨቋኝ እንዲሁም ጠላትና ወዳጅ ብሎ የለየ ፍጹም ልዩነት የሚጎላበት እንደሆነ ገልፀዋል።
ሁለቱም ትርክቶች ለሀገር የማይበጁ ነጠላ ትርክት በመሆናቸው ለተቃርኖ፣ ለአመጽ፣ ለጽንፈኝነት፣ ለጥላቻና ለመከፋፈል በር ከፋች ናቸው ብለዋል።
በዚህም ባለፉት ሥርዓቶች ውስጥ የነበሩ ነጠላ ትርክቶች የጋራ እሴቶችን ከማዳበር ይልቅ ትናንት ላይ በማተኮር ኢትዮጵያ እንደ ዕድሜዋ ጠንካራ ሀገር እንዳትሆን ማድረጉን ገልፀዋል።
ከዚህ አኳያ መደመር የትላንት፣ የዛሬና የነገ ገዥ ምዕራፎችን በማስተሳሰር አሰባሳቢ የሆነ ብሔራዊ ትርክት እንደሚያስፈልግ ያምናል ነው ያሉት።
ብሔራዊ ትርክት ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።
የትናንትን ዕዳና ምንዳ በመለየት ለነገ ትውልድ የተሻለ ሀገር መገንባት ላይ የተንተራሰ፣ ለብሔር ማንነት፣ ለሀገራዊ አንድነት እና ለብዝኃነት እኩል ቦታ የሚሰጥ፣ ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት እሳቤን ባቀፈ መልክ ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት የሚል ግብ እንዳለውም ገልፀዋል።
የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክና እሴቶች ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት የሚያስችል ትርክት መሆኑን ተናግረዋል።
አድዋን መሰል አስተሳሳሪ ትናንትንና የሕዳሴ ግድብን መሰል አስተሳሳሪ ነገን በማጉላት አንድነትን በሚያጠናክር መልክ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አፍራሽ ትርክቶችን መገዳደር፣ ህዝበኝነትን መዋጋት፣ የኃይልና አመጽ መንገዶችን በጋራ መዋጋት እንደሚያስፈልግና ለወል ትርክት ግንባታው ሁሉም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።