ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብን ከደለልና መጤ አረም መከላከል የሚያስችሉ የተፋሰስ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል- ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከደለልና ከመጤ አረም መከላከል የሚያስችሉ የተፋሰስና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ 12 ተፋሰሶች ያሉ ሲሆን እነዚህ ተፋሰሶች ለአገሪቱ ብሎም ተፋሰሱ ለሚያቋርጥባቸው አገራት የውኃ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

ይሁንና አብዛኞቹ ተፋሰሶች የደለልና የመጤ ወራሪ አረም ስጋት የተጋረጠባቸው መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአሁን ጊዜ እምቦጭ በሁሉም የውኃ አካላት ላይ መከሰቱንና ይህንንም ለመቆጣጠርና ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውኃ ኃብት አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ በላይነህ ይርዳው የገለጹት።

ሚኒስቴሩ ሕብረተሰቡን በማስተባበር እያከናወነ ያለው የተፋሰስና የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ሥራ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ከማድረግ ባለፈ ለመጤ ወራሪ አረሞች ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከደለልና ከመጤ አረም መከላከል የሚያስችሉ የተፋሰስ እንክብካቤ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ነው የተናገሩት።

እንደ አቶ በላይነህ ገለፃ፣ አባይ፣ አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ገናሌ ዳዋና ኦሞ ጊቤ ተፋሰሶች የውኃን ደኅንነት መጠበቅ የሚያስችላቸውን አንድ ዕቅድ አውጥተው ተግባራዊ እያደረጉ ነው።

በዕቅዱ ተፋሰሶችን ከደለልና ከመጤ አረም እንዲሁም ከብክለት ለመከላከል ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም