ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተባበርን ተግዳሮትን አሸንፈን ለድል መብቃት እንደምንችል ትልቅ ማሳያ ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ ፤መጋቢት 24/2016 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተባበርን የትኛውንም አይነት ተግዳሮት አሸንፈን ለድል መብቃት እንደምንችል ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት 13ኛ ዓመት "በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተከብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንደ ሀገር የትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢገጥመንም  ከተባበርን  በድል እንደምንወጣው ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ  አሁን ላይ  95 ነጥብ 8 በመቶው መድረሱን ተናግረው፤ለዚህ መድረሱም የለውጡ መንግስት የአመራር አሰጣጥና የህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ  መሆናቸውን  አመላክተዋል።

ታሪካዊ ጠላቶቻችን የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎል ምክንያቶችን በመደርደር ሊያስቆሙን ቢሞክሩም እንዳሰቡት ግን አልሆነላቸውም ብለዋል።

ይህም የሆነው ህዝብና መንግስት በአንድነትና በትብብር መስራት በመቻላቸው መሆኑን ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም