የመደመር እሳቤ ከፍጹም ልዩነትና ፍጹም አንድ አይነትነት ወደ ሀገራዊ አንድነት የሚያሰባስብ አዕማድ እና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የዕይታ አድማስ ያሰፋ ነው-የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ ከፍጹም ልዩነትና ፍጹም አንድ አይነትነት ወደ ሀገራዊ አንድነት የሚያሰባስብ አዕማድ እና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የዕይታ አድማስ ያሰፋ ነው-የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
ሐረር ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦የመደመር እሳቤ ከፍጹም ልዩነትና ፍጹም አንድ አይነትነት ወደ ሀገራዊ አንድነት የሚያሰባስብ አዕማድ እና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የዕይታ አድማስ ያሰፋ ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
ኢዜአ ከሐረሪ ክልል ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የመደመር ጉዞ የፓናል ውይይት ‘የለውጡ ትሩፋቶችና መደመር’ በሚል መሪ ሃሳብ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የመደመር እሳቤ የመጪውን ትውልድ ጥቅም እና ፍላጎት ማሳካት ላይ ያተኮረ፣ በህዝብ ባህልና አኗኗር የተሳሰረ፣ በቀጣናውና በአፍሪካ የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እንዲጠናከር ያስቻለ የሕልውናችን መነሻ ነው።
የመደመር ዕሳቤ በሃሳብም ሆነ በተግባር አካታችና ሁሉን አቀፍ፣ ኢትዮጵያዊነትና የብሄር ማንነት ሚዛን የሚያስጠብቅ፣ አብሮነት፣ ትብብር፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን የሚያጠናከር ነው ብለዋል።
መደመር ፍጹም አንድ አይነትነትና ፍጽም ልዩነት ላይ ያተኮሩ ዕሳቤዎችን የሚያስታርቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ እንዲሰባሰቡ እና ለተግባራዊነቱ እንዲተጉ መንገድ የከፈተና የዕይታ አድማስ ያሰፋ እሳቤ የመሆኑንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ መሪነት ከመጡ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ሀገሪቷ ተዘዋውረው የመደመር ዕሳቤ ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ እንደሆነ መናገራቸውን አስታውሰዋል።
የመደመር ዕሳቤዎችን መነሻ በማድረግ የጻፏቸው ሶስት መፃሕፍት ከትናንት ተምረን፣ የዛሬን ዕድል አይተን፣ የነገ መዳረሻን ለመቃኘት የሚያስችሉ ፍልስፍና ተኮር ዕይታዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከለውጡ ወዲህ እንደ ሀገር ያሉ ፀጋዎችን በማልማት ውጤታማ መሆን የተቻለበት፣ በስንዴ ልማት በተሰሩ ስራዎች ዓለም ዕይታውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለከት የተደረገበት ነው ብለዋል።
የሀረር ከተማ የጀጎል ግንብና ሸዋል ኢድን ጨምሮ በዓለም የታወቁ የቱሪዝም ጸጋዎችን የታደለች፣ ከሰሃራ በታች ብቸኛዋ የቅርስ ከተሞች አባል የሆነች፤ የሰላምና አብሮነት ከተማ እና የመደመር ዕሳቤ ተምሳሌት መሆኗን ገልጸዋል።
በመደመር እሳቤ ላይ ትኩረት ያደረጉ መሰል መድረኮች እምቅ የቱሪዝም ጸጋዎችን በማልማት ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ለማዋል ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ለውጡ ሀገር የሚያጸኑ ጠንካራ ተቋማት መገንባት የተቻለበት መሆኑን ገልጸው፣ የተገኙ ስኬቶች ስር እንዲሰዱ እና ዕሳቤው ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር ለውጡን ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
መደመር እንደ ሐረሪ ክልል ወንድማማችነት እንዲጎለብት ያስቻለ በመሆኑ በመደመር ዕሳቤ አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ከሴራ ወደ መርህ ተኮር ስርዓት፣ ከስርዓት አልበኝነት ወደ ሕግ የባላይነት፣ ከቀውስና ግጭት ወደ ሰላምና መረጋጋት፣ ከመጋፋፋት ወደ ዕርቅና አብሮነት መሸጋገር የተቻለበት መሆኑንም ገልጸዋል።
በለውጡ ስድስተኛ ዓመት መሰል ፓናል ስናካሂድ የመደመር ሀገራዊ ዕሳቤን ወደ መድረክ አምጥቶ በማጠናከር፣ ድላችንን የምናስቀጥለበትና ወደፊት ለመራመድ ቃላችን ለማደስ በማለም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፣ የለውጡ ስኬቶች በሚዘከሩበት ዕለት የመደመር ተምሳሌት በሆነችው ሐረር ከተማ ፓናል ውይይት መካሔዱ ትልቅ መልዕክት አለው ብለዋል።
የመደመር ጉዞ የፓናል ውይይት በመደመር ዕሳቤ ዙሪያ የሀሳብ ሜዳ በማዘጋጀት ሀገራዊ አንድነትና አብሮነት በማጠናከር የዕይታ ጽናት የመፍጠር ዓላማ ያለው እንደሆነም ገልጸዋል።
ኢዜአ ሀገራዊ ገፅታ የመገንባት፣ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅም እንዲከበር የበኩሉን ሚና መጫወቱን አጠናክሮ እንደሚቀጠል ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያበረከቷቸው መፃሕፍት ዕውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊነትና አንድነት እንዲጠናከር የሚያስችሉ በመሆናቸው ለተግባራዊነቱ ኢዜአ መሰል ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጠል አረጋግጠዋል።