በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ኢኒስቲትዩት ሊቋቋም ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ኢኒስቲትዩት ሊቋቋም ነው
አዲስ አበባ ፤መጋቢት 24/2016 (ኢዜአ)፦የተመሰከረላቸው ሒሳብ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ኢኒስቲትዩት ሊቋቋም መሆኑን የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ጨምሮ ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማትን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ የሚያስችል አሠራር እየዘረጋች ነው።
ከዚህ ባለፈም አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናና ሌሎችንም አህጉር አቀፍ ስምምነቶችን ገቢራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፤ የዓለም አቀፉ ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ሁሉን አቀፍ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ አጎናፍር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ለመግባት የጀመረችው ጥረት የሚበረታታና የሚደገፍ ነው።
እንዲያም ሆኖ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና ባለኃብቶች በካፒታል ገበያም ሆነ በሌሎች የፋይናንስ ዘርፎች ለመሰማራት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት ይፈልጋሉ ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም የተመሰከረላቸው ሒሳብ ባለሙያዎች በብዛትም በጥራትም ያስፈልጋሉ ብለዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው የሒሳብ አያያዝ ትምህርት እና ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አሠራር የሚጣጣም አይደለም ያሉት አቶ ፍቃዱ የኢኒስቲትዩቱ መቋቋም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አሠራር መስፈርቶችን የሚያሟሉ የተመሰከረላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያግዝ እንደሆነም አክለዋል።
የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ተቆጣጣሪ አካል ሆኖ ሳለ የብቃት ማረጋገጫ የመስጠት ሚናን መውሰዱ ተገቢ አሠራር አይደለም ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ችግሩን ለመፍታት በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎችን የሚያፈራና የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጥ ኢንስቲትዩት ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢኒስቲትዩቱን ለማቋቋም የባለድርሻ አካላት ሀሳብ በግብዓትነት የተካተተበት የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሕግ ማዕቀፉ በፍትሕ ሚኒስቴር ተገምግሞ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ቁጥር ከ600 አይበልጡም ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኢኒስቲትዩቱ መቋቋም የባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በኢኒስቲትዩቱ ባለሙያዎች ከንድፈ-ሀሳብ ባሻገር የተግባር ሥልጠናዎች በመውሰድ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት ዕድል እንደሚያገኙም አብራርተዋል።
ከኢኒስቲትዩቱ የሚወጡ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች የት ናቸው? በተሰጣቸው ፈቃድ መሠረት እየሰሩ ነው ወይ? የሙያ ሥነ-ምግባራቸው ምን ላይ ነው? በሚሉ ጉዳዮች ክትትል ማድረግ የሚያስችል አሠራር እንደሚዘረጋም ገልፀዋል።
ኢኒስቲትዩቱን ለማቋቋም የተዘጋጀው የሕግ ማዕቀፍ ለኢትዮጵያ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችን ይዟል ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በተለይም በተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች እጥረት ምክንያት የካፒታል ገበያና ሌሎች ዓለም አቀፍ ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓቶች አተገባበር እንዳይስተጓጎል በማድረግ ረገድ የኢኒስቲትዩቱ መቋቋም ትልቅ እፎይታ እንደሚሆን አስረድተዋል።