ቀጥታ፡

በሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ለፈተናዎቻችን ሳንንበረከክ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ በሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ለፈተናዎቻችን ሳንንበረከክ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ተደምረን የጀመርነውን ጉዞ ዳር ለማድረስ በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የለውጡ ፍሬያማ ጉዞ ለተጀመረበት 6ኛ ዓመት እና የኢትዮጵያዊነት መሰረት ለሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ 13ኛ ዓመት እንኳን አደረሣችሁ፤ አደረሰን ብለዋል።

በመልዕክታቸውም በለውጡ መሃንዲስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተመራው የለውጥ ኃይል በብዙ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተና ውስጥ ሆኖ በርካታ ስኬቶችን በመጎናጸፍ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከእነዚህም መካከል የህዳሴ ግድባችን ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረስ፣ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ለብሳ ከስንዴ አስመጭነት ወደ ላኪነት የተሸጋገረችበት መሆኑን አስታውቀዋል።

የለውጡ አመታት ከ128 አመታት በኋላ የአድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ ተጠናቆ የተመረቀበት፣ ከተማችን አዲስ አበባ ትኩረት አግኝታ በርካታ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል መሆን የጀመረችበት እና በሰው ተኮር ስራዎቻችን ማኅበራዊ ፍትህ ያነገስንበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለውም ቃል በተግባር ተመንዝሮ ኢትዮጵያችን በሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት የደመቀች፤ ዕድገቷ መፋጠን የጀመረበት፣ በመፍጠንና በመፍጠር ዕዳዋ እየቀነሰ ምንዳዋ እየጨመረ የመጣች ሀገር እየሆነች ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ለፈተናዎቻችን ሳንንበረከክ ከችግሮቻችን ባሻገር የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ተደምረን የጀመርነውን ጉዞ ዳር ለማድረስ በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

ምድራዊ ሃይል ሊያስቆመው የማይችለውን የብልጽግና ጉዞ ገብቷችሁ ድጋፋችሁንና ደስታችሁን ለገለፃችሁ ምስጋናዬን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ ብለዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም