በ45ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ አትሌቶች አቀባበል ተደረገ

228

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው 45ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ አትሌቶች በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ በመገኘት አቀባበል ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ናቸው።


 

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና ሌሎችም የፌዴሬሽን አመራሮች በመገኘት ለአትሌቶቹ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው የ45ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት ምድቦች ማለትም 8ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ወንዶች፣ 6 ኪሎ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ሴቶች፣ 4x2 ኪሎ ሜትር የድብልቅ ሪሌ ሴት/ወንድ፣ የ10 ኪሎ ሜትር የአዋቂ ሴቶች እና አዋቂ ወንዶች በተካተቱበት ውድድር ከ51 ሀገራት 485 የሚሆኑ አትሌቶች ተፎካክረውበታል።

በዚህም ውድድር ኢትዮጵያ በ14 ሴት እና በ14 ወንድ በ28 አትሌቶች የተወከለች ሲሆን በሁለት ወርቅ፣ በስድስት ብር እና በሁለት ነሃስ በአጠቃላይ በ10 ሜዳሊያ ከዓለም የሁለተኛነት ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቃለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም