የመደመር ጉዞ የፓናል ውይይት "የለውጡ ትሩፋቶችና መደመር" በሚል መሪ ሃሳብ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር ጉዞ የፓናል ውይይት "የለውጡ ትሩፋቶችና መደመር" በሚል መሪ ሃሳብ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፤መጋቢት 24/2016 (ኢዜአ)፦የመደመር ጉዞ የፓናል ውይይት "የለውጡ ትሩፋቶችና መደመር" በሚል መሪ ሃሳብ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ''የመደመር ጉዞ'' የፓናል ውይይት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች ሲካሄድ እንደነበር ይታወቃል።
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱ፣ በጅግጅጋ፣ በአሶሳ፣ በሆሳዕና፣ በድሬዳዋ፣ ቦንጋን ጨምሮ በስምንት ከተሞች የተካሄደ ሲሆን ዘጠነኛው ዙር መርሐ ግብርም በዛሬው እለት በሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በፓናል ውይይቱ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ምሁራንና የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ታድመዋል።
"የለውጡ ትሩፋቶችና መደመር" በሚል መሪ ሀሳብ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ባለው የፓናል ውይይት ያለፉት ስድስት ዓመታት ለውጦች ከመደመር እሳቤ ጋር ተሰናስለው ለውይይት ቀርበዋል።
የዛሬው ፓናል ያለፉት ስድስት ዓመታት የለውጥ ትሩፋቶች፣ የገዥ ትርክት እና የመደመር እሳቤዎች ላይ በማጠንጠን የፍቅር፣ የአብሮነት፣ የመቻቻል እና ሰላም ተምሳሌት በሆነችው ሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የመደመር ጉዞ የፓናል መድረኮች በመደመር እሳቤና ትሩፋቶች ላይ ተንተርሰው በተለያዩ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮች እና ዐውዶች ጋር እየተሰናሰሉ የሚዘጋጁ ናቸው።