ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ የሚያስፈልገውን የኢነርጂ መሰረት በመገንባት ሀገራዊ ብልጽግና መፍጠር የሚያስችለን ወሳኝ ተግባር ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2016(ኢዜአ)፦ የህዳሴ ግድብ የሚያስፈልገውን የኢነርጂ መሰረት በመገንባት ዕድገት፣ ብልጽግና እንዲሁም ሀገራዊ ሀብት መፍጠር የሚያስችለን ወሳኝ ተግባር ነው ሲሉ አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ተናገሩ። 

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት ‘በህብረት ችለናል’ በሚል መሪ ሀሳብ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከብሯል። 

በበዓሉ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የተለያዩ አደረጃጀት አመራሮች እንዲሁም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ለህዳሴ ግድቡ አስተዋጽኦ ያደረጉ እና የዳያስፖራ አባላት ተሳትፈዋል። 


 

በበዓሉ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የህዳሴ ግድባችን ሁሉም ዜጋ ሀብቱን፣ ዕወቀቱንና ጊዜውን በማስተባበር የሚገነባ ልዩ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡ 

ግንባታው የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ብሎም  ለህዝቦቿ የሚያስፈልገውን የኢነርጂ መሰረት በመገንባት ዕድገት፣ ብልጽግና እንዲሁም ሀገራዊ ሀብት መፍጠር የሚያስችለን ወሳኝ ተግባር ነው ሲሉም ገልፀዋል። 


 

ፕሮጀክቱ ከጅምሩ አንስቶ እስካሁን ድረስ ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን እና ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ የዳያስፖራ አባላት ምስጋና አቅርበዋል።

አምባሳደር ስለሺ በቀለ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ይኸው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል።

በዕለቱ ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም መካሄዱን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም