ቀጥታ፡

የዴሞክራሲ ተቋማት የህዝቡ ቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ የጀመሩትን ጥረት ማጠናከር አለባቸው - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ጋምቤላ፤ መጋቢት 23/2016(ኢዜአ)፦ የዴሞክራሲ ተቋማት ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ የጀመሩትን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።

ቋሚ ኮሚቴው በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ አምስት የዴሞክራሲ ተቋማት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል። 

ቋሚ ኮሚቴው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችን ጎብኝቷል።


 

የቋሚ ኮሚቴው አባልና የቡድኑ አስተባባሪ አቶ ከድር እንድሪስ እንደገለጹት በጉብኝታቸው ተቋማቱ በሀገሪቱ እየተካሄዱ የሚገኙ የልማት፣ የዴሞክራሲና ሌሎች ስራዎች እንዲሳለጡ የተጣለባቸውን ተልዕኮ እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት ተቀናጅተው በመስራት ረገድም መልካም ጅምሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ተቋሟቱ በቀጣይ የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነትና ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡ ቅንጅታዊ አሰራሮቻቸውን እንዲያጠናክሩ ኮሚቴው ግብረ መልስ መስጠቱንም ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ቅርንጫፎችም ከህዝብ የሚነሱ ቅሬታዎች እርምት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ተመስገን አምባቸው ናቸው።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር እያደረጋቸው ያሉት ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተቋማቱ የጀመሩትን ስራ የበለጠ ማጠናከር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቤል አዳነ፣ የተሰጣቸውን ግብረ መልስ ተቀብለው ለተሻለ አፈፃፀም እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በተለይም ተቀናጅቶ በመስራት በኩል ያሉትን ክፍተቶች ለማረም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በትጋት ይሰራል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታጠቅ ተፈራም እንዲሁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የጋራ መድረክ በማጠናከር በኩል ጽህፈት ቤቱ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ በሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት ምልከታ ያደረገው ዛሬን ጨምሮ ላለፉት ሶስት ቀናት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም