ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ትሠራለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ትሠራለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እንደምትሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችን ያካተተ ልዑክ በሳዑዲ አረቢያ የሥራ ጉብኝት አድርጓል።
አቶ ተመስገን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሳዑዲ ዓረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን የላኩትን መልዕክት በዛሬው ዕለት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስረክበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳዑዲ አረቢያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፈርሃን ጋር የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር በኢኮኖሚ፣ በጸጥታ እና በሰው ኃይል ሥምሪት ያላትን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እየሠራች መሆኑን በውይይቱ ወቅት አቶ ተመስገን ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ የጋራ ኮሚሽን ሥብሰባ ማካሄድ፣ በሂደት ላይ ያለውን የሞያተኛ የስራ ሥምሪት ስምምነት መፈራረም እና በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ ያለውን ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ልዑኩ የኢትዮጵያ ሕጋዊ የባሕር በር ጥያቄ በቀጣናው ለሚካሄደው የምጣኔ ሀብት ውህደት ስለሚኖረው ጠቀሜታ ገለጻ አድርጓል።
የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፈርሃን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሳል አመራር እያስመዘገበች ያለውን እድገት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ለሳዑዲ-አፍሪካ ግንኙነት ድልድይ እና ወሳኝ ሀገር ነች ያሉት ልዑል ፋይሰል ቢን ፈርሃን የሁለቱ ሀገሮች በሁሉም መስክ መተባበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱ ወገኖች በወቅታዊው የቀጣናው ሰላም ሀሳብ በመለዋወጥ በአካባቢው ሰላምና ደኀንነት እንዲሰፍን ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ማንሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።