የህብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል- አቶ አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የህብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል- አቶ አረጋ ከበደ
ባህር ዳር ፤ መጋቢት 23/2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የህብረት ሥራ ማህበራትን አሰራርና አደረጃጀት በማዘመን ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ለተጀመረው ሪፎርም ሁሉም እገዛ ማድረግ እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አስገነዘቡ።
''የህብረት ሥራ ሪፎርም ከማደራጀት ባሻገር!'' በሚል መሪ ሀሳብ ክልላዊ የሪፎርም ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የህብረት ሥራ ማህበራት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት አይተኬ ሚናቸውን እየተወጡ ነው።
ለዚህም ማህበራቱ አርሶ አደሩ ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቅ፣ አምራቹንና ሸማቹን በማገናኘት እንዲሁም የምርት ግብዓቶችን ተደራሽ በማድረግ ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት በማቋቋም ለአባሎቻቸው በአነስተኛ ወለድ ብድር ተደራሽ በማድረግ የአባሎቻቸውን ጥቅምና መብት ለማስከበር እየሰሩ መሆኑንም አቶ አረጋ አስታውቀዋል።
ማህበራቱ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሪፎርም ሥራ ተጨባጭ ውጤት ሊያመጣ በሚችል አግባብ እንዲተገበር ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግስትም ለሪፎርሙ ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያረጋገጡት።
የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ በበኩላቸው በሀገሪቱ ከ28 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሏቸው 110 ሺህ የህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ማህበራቱ በአገር ኢኮኖሚ የጎላ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ያሉባቸውን የአደረጃጀት፣ የአሰራርና የአመራር ችግሮች ለመፍታት ሪፎርም እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የተጀመረው ሪፎርም እንዲሳካም የህብረት ሥራ አመራሮች ከአባላት ጋር ግልፅ ውይይት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ምክትል ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማገዝ የህብረት ሥራ ማህበራት ሚናቸው ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው።
የህብረት ሥራ ማህበራት በተለያዩ ዘርፎች ተቋቁመው እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም በአመለካከት፣ በፋይናንስና በተማረ የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት የሚፈለገውን ለውጥ እንዳላመጡ ተናግረዋል።
ማህበራትን መልሶ ማደራጀት ያስፈለገው የተበታተነ አቅማቸውን በማሰባሰብና በማጎልበት በገበያው መሪ ተዋናይ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑን ዶክተር ድረስ አስረድተዋል።
በመሆኑም ማህበራትን መልሶ ለማደራጀት የተጀመረው ሥራ ውጤታማ እንዲሆን በየደረጃው የምንገኝ አመራሮች ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በአማራ ክልል ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሏቸውና በተለያዩ ዘርፎች የተደራጁ 23ሺህ የህብረት ሥራ ማህበራት እንደሚገኙም ተመላክቷል።
በመድረኩ የክልሉና የዞን የሥራ ኃላፊዎች፣ የህብረት ሥራ ማህበራት አመራር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።