ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ለባለሀብቶች የሚደረገው ድጋፍ ይጠናከራል - ኮሚሽነር ሀና አርዓያስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ለባለሀብቶች የሚደረገው ድጋፍ ይጠናከራል - ኮሚሽነር ሀና አርዓያስላሴ
ደሴ ፤ መጋቢት 23/2016(ኢዜአ)፦ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ለባለሀብቶች የሚደረገው ድጋፍ የሚጠናከር መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀና አርዓያስላሴ ተናገሩ።
በኮሚሽነር ሀና አርዓያስላሴ የተመራ ቡድን የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የስራ እንቅስቃሴን ተመልክቷል።
ኮሚሽነር ሀና በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት ጥረት እየተደረገ ነው።
በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክም በባለሃብቶች የሚነሱ የመሰረተ ልማት፣ የገበያ ትስስር፣ የግብዓት አቅርቦትና ሌሎችንም ክፍተቶች ለማስተካከል ቅንጅታዊ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በዚህም ኢንዱስትሪዎቹ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲተኩ ከማድረግ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፤ በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማነቃቃት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲተኩና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በ2015 ዓ.ም በ565 ሚሊየን ብር ወጪ የኢንዱስትሪዎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ መደረጉን አስታውሰው፤ ዘንድሮም በ297 ሚሊዮን ብር መሰረተ ልማት የማሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የ'ባቱ ትሬዲንግ' ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋየ ሞላ በበኩላቸው፤ በቀን እስከ 10 ሺህ ኪሎ ግራም ክር ማምረት አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል።
በቀጣይም ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የሰጠው ትኩረትና ድጋፍ የበለጠ እንድንሰራ አድርጎናል ብለዋል።
በጉብኝቱ የክልልና የኮምቦልቻ ከተማ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ውይይትም ተካሄዷል።