በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን - የብልጽግና ፓርቲ አመራርና አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን - የብልጽግና ፓርቲ አመራርና አባላት
ባህር ዳር ፤ መጋቢት 23/2016 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ሲሉ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ አመራርና አባላት ገለጹ።
በባህር ዳር ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው የብልጽግና ፓርቲ አመራርና አባላት ክልላዊ ኮንፈረንስ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ዛሬ ተጠናቋል።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው በንባብ ባሰሙት የአቋም መግለጫ እንደተመለከተው፤ በየትኛውም አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሰላማዊ አማራጭ ብቻ መፍታት ይገባል።
በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ መፍትሄ እንዲያገኝ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ በመግለጫው ተገልጿል።
በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን ጥረት እንደሚደረግ በአቋም መግለጫው ተጠቁሟል።
ህብረ ብሄራዊ አንድነትንና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገንባት የላቀ አገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ በትኩረት እንደሚሰራም ተመልክቷል።
ከዚህ ጎን ለጎን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረትን ለመከላከል የግብርናና ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት በማሳደግ ምርት በዓይናትና በብዛት ለማቅረብ ርብርብ እንደሚደረግ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች አረጋግጠዋል።
በማህበራዊ የልማት ዘርፉም የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ከማስፋት ባሻገር በጤና ረገድም በሽታን መከላከል ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰሩም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
የመንገድ፣ የየኤሌክትሪክ ሃይል፣ የመስኖ፣ የቴሌኮምና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ፍትሃዊነታቸውንና ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወኑ አመራርና አባላቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ባቀረቡት የአቋም መግለጫ አረጋግጠዋል።
በመሆኑም የአስተሳሰብ ልዩነቶች በዜጎች ሁለንተናዊ ደህንነትና በሃገር አንድነት ላይ የስጋት ምንጭ የሚሆኑበት ምዕራፍ እንዲያበቃ በቁርጠኝነት እንታገላለን ሲሉ ተሳታፊዎች በአቋም መግላጫቸው ገለፀዋል።
መላው የክልሉና የኢትዮጵያ ህዝብና የፓርቲው ደጋፊዎች የብልጽግና ጉዞን በማሳለጥ የበለፀገች አገርን ለመገንባት የተጀመረው ጥረት ዳር እንዲደርስ ከድርጅቱ ጎን እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበዋል።