በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በተካሄደ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በተካሄደ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል - ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2016(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው በጀት ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ በተካሄደ ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ መልማቱን ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።
በኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት በሚደርስ የአፈር መሸርሸር በየዓመቱ እስከ 2 ቢሊየን ቶን አፈር እንደምታጣ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የአፈር መሸርሸር ችግርን ለመቀነስም በየዓመቱ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ቀጣይነት ያለው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እየተከናወነ ይገኛል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፋኖሴ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት የአፈር መጠበቅ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና አለው።
በተለይም ለሰብል ምርታማነት ማደግ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው በማንሳት፥ ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ለማሳለጥ ያግዛል ነው ያሉት።
በመሆኑም በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት አርሶ አደሩን በማሳተፍ ከጥር ወር ጀምሮ ሀገር አቀፍ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመከናወን ላይ እንደሆነም አንስተዋል።
በሁሉም ክልሎች በ6 ሺህ 200 ተፋሰሶች ላይ ከ2 ሚሊዮን 250 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በዚህም እስካሁን በተከናወነው የልማት ስራ ከ2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ መልማቱን ጠቅሰዋል።
የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ የግብርና ምርታማነትን ለማስቀጠል የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራ ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኘ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የነጠፉ ወንዞች ውሃ እንዲዙ፣ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ እና የአፈር ለምነት እና የደን ሽፋን እንዲጨምር እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት በተፋሰስ ልማት ስራ ላይ ህብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ ይበልጥ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱንም አብራርተዋል።