የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካና በአውሮፓ ሦስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎችን በቅርቡ ለመክፈት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካና በአውሮፓ ሦስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎችን በቅርቡ ለመክፈት እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2016(ኢዜአ)፦ በአፍሪካና በአውሮፓ ሦስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎችን በቅርቡ ለመክፈት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ በዕቅዱ መሠረት የአውሮፕላን ቁጥሮችን እየጨመረ አዳዲስ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን እያሰፋ ይገኛል ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ በርካታ አውሮፕላኖችን ከቦይንግ ኩባንያ ለመግዛት ሥምምነት ያደረገ ሲሆን፤ ከኤር ባስ ኩባንያም በትዕዛዝ ላይ ያሉ አውሮፕላኖች መኖራቸውን አስታውሰዋል።
አየር መንገዱ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ መዳረሻዎቹን በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን ጠቁመው፤ በቅርቡ በሴራሊዩን ፍሪታውን፣ በፖላንድ ዋርሶው እንዲሁም በቦትስዋና ከተማ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎችን ለመክፈት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ተጨማሪ መዳረሻዎችን ማስፋት እንደ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የያዘው ግብ መሆኑን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በዕቅድ ውስጥ የሌሉ መዳረሻዎችንም አዋጭነታቸው ታይቶ ወደ ሥራ እንደሚያስገቡ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበጀት ዓመቱ ባስቀመጠው ዕቅድ መሠረት በመጀመሪያዎቹ ወራት ሊበርባቸው ያቀዳቸውን አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች ማሳካቱንም ተናግረዋል።
ለአብነትም፣ በእንግሊዝ የለንደን ጋትዊክ፣ በስፔን ማድሪድና በመካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ ባንጉዊ አዳዲስ መዳረሻዎች ተከፍተው ለመንገደኞች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎችን በማስፋት አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን አስጠብቆ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም አየር መንገዱ 136 ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ሲሆን፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 ያሉትን የአውሮፕላኖች ቁጥርና መዳረሻዎችን በእጥፍ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።