ቀጥታ፡

የለውጡ መንግሥት ብዙ ፈተናዎች የነበሩበትን የሕዳሴ ግድብ  ግንባታ በከፍተኛ እምርታ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እንዲደርስ አድርጓል - አምባሳደር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2016(ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግሥት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የነበሩበት በርካታ ተግዳሮቶች ላይ ማስተካከያ በማድረግ ግንባታው በከፍተኛ እምርታ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እንዲሻገር ማድረጉን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የሕዳሴው ግድብ ዋና ተደራዳሪ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ገለጹ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መጣሉ ይታወቃል።

ይህም የኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት የነበረውን የአባይ ወንዝን ወደ ብርኃን ለመቀየር በቁርጠኝነትና በአንድነት የተነሱበት ታሪካዊ ቀን መሆኑም እንዲሁ። 

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የሕዳሴው ግድብ ዋና ተደራዳሪ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ግንባታ የተጀመረበት መንገድ መልካም የሚባል እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይሁንና በግንባታው ሂደት የተለያዩ መሰናክሎች ማጋጠማቸውን ጠቅሰው የፕሮጀክት አስተዳደር ላይ የነበሩ መሰረታዊ ችግሮች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።


 

የፕሮጀክት አስተዳደር ሥራው ለአገር ውስጥ ተቋራጭ የተሰጠበት መንገድ ትክክለኛ አካሄድን ያልተከተለና ውስብስብ መሆኑ የግድቡ ሥራ የሚፈልገውን የካበተ ልምድና እውቀት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደነበር ገልጸዋል። 

በዚህም ምክንያት ግንባታው መጓተት እንዳጋጠመው አመልክተዋል።

በወቅቱ የኮንክሪት ግንባታው በፍጥነትና በተያዘለት ጊዜ ቢከናወንም የኤሌክትሮ መካኒካልና ብረታ ብረት ሥራው በመጓተቱ የግድቡ ግንባታ እንዳይሳካ ፈተና እንደነበር ገልጸዋል።

የለውጡ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጉዳዩ ላይ በጥልቀት በመወያየት ያደረጋቸው የማስተካከያና የማሻሻያ ሥራዎች የግድቡ ግንባታ እንዲፋጠን ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ሕዝቡ በራስ አቅም ግድቡን ለመገንባት ያሳየው ቁርጠኝነትና በተግባር ያደረገው ድጋፍ ለግድቡ ግንባታ መፋጠን ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጉንም ተናግረዋል።    

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ አፈጻጸም ከ95 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸው ይህም ትልቅ እምርታ መሆኑን ነው አምባሳደሩ ያብራሩት። 

በተያዘው ዓመት መጨረሻ ድረስ የኮንክሪት ሥራው እንደሚጠናቀቅ ገልጸው አምስት ተጨማሪ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች እስከ ታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም ደረጃ በደረጃ ወደ ሥራ እንደሚገቡ አብራርተዋል።

የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን የኃይል አቅም በ130 ፐርሰንት እንደሚያሳድግ ጠቁመው ይህም የአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ ለጎረቤት አገራት ኤሌክትሪክ በመሸጥ ገቢ ማግኘት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ በአሁኑ ሰዓት የያዘው የውኃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ አጠቃላይ የውኃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ያድጋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም