ቀጥታ፡

ለኮሚሽኑ ሥራዎች ስኬታማነት ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ 

ሐረር ፤ መጋቢት 23/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ልዩነት ሲፈጥሩና ላለመግባባት ምክንያት የነበሩ አጀንዳዎች ላይ በጋራ ተወያይቶ ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መሀመድ ሀሰን እንደገለጹት ኢትዮዽያዊያን አብሮ በጋራ የመኖር፣ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶች እንዳሏቸው ሁሉ ልዩነቶችም ጎልተው ሲንጸባረቁ ይታያል።

በየዘመናቱ በህብረተሰቡ መካከል ላለመግባባትና ለልዩነት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን ፈትቶ የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር እንደማህበረሰብም ሆነ እንደሀገር ሁሉን ያካተተ ሰፋያለ ምክክር ከእዚህ ቀደም አለመደረጉን አስታውሰዋል።

ዶክተር መሀመድ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በየደረጃው ለማካሄድ የታሰበው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አካታች በመሆኑ ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ፋይዳው የጎላ ነው። 

ለዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ ውስብስብ ችግሮችንና አለመግባባቶችን በመፍታት ዘላቂ መፍትሄ ከማምጣት ባለፈ ኢትዮዽያን ወደተሻለ የእድገት ደረጃ ለማድረስ ያግዛል ሲሉም ገልጸዋል።

በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመወያየት ባህልን ከማጎልበት ባለፈ ልማትና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የራሱ አስተዋጾ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

እንደ ዶክተር መሀመድ ገለጻ የማያግባቡና ልዩነት የሚያሰፉ ትርክቶችን በማስወገድ መፍትሄ የሚያስገኝ አሰባሳቢ የጋራ ትርክትን ለማጎልበት ሀገራዊ ምክክሩ የጎላ ጠቀሜታ አለው።

በመሆኑም ሁሉም ለምክክር ኮሚሽኑ ሥራዎች ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ረታ ድጉማ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የማያግባቡ ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ሁሉን ያካተተ ውይይት አለመከናወኑን አስታውሰው፣ ኮሚሽኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ ወሳኝ ሀገራዊ ችግሮች እንዲፈቱ የጀመራቸው ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል።

ዶክተር ረታ እንዳሉት እንደሀገር የሚደረገው ምክክር ለዘመናት በዜጎች መካከል ልዩነትን ሲፈጥሩ የነበሩ ወሳኝ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው።

ትውልዱ ችግሮችን በውይይትና በንግግር የመፍታት ባህልን እንዲያዳብር ከማድረግ አንጻር የራሱ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉም አመልክተዋል።

ልማት እንዲፋጠን የማያግባቡ ጉዳዮችን በውይይት የመፍታት ባህል ሊጎለብት ይገባል ያሉት ዶክተር ረታ፣ ኮሚሽኑ ሀገራዊ አንድነት እንዲመጣ ለጀመራቸው ሥራዎች ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የኢትዮዽያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰሞኑን በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ የማህበረሰብ ተወካይዮችን ልየታ ማካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም