የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል አለብን- የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል አለብን- የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 22/2016(ኢዜአ)፦ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ ጥሪ አቀረቡ።
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰረት የተቀመጠበት 13ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩም የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ጨምሮ የሸገር ከተማ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ታዋቂ አትሌቶችና ከሸገር ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን ጠብቀው ለአገር ብልጽግና በጋራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል
የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተሰጠው በሳል አመራር ወደ መጨረሻ ምዕራፍ ለተሸጋገረው ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸውንም ነው ያነሱት፡፡
የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በክልሉ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በለውጡ የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል የተጀመረውን ብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሁሉም መስክ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ስራም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያዊያን በመተባበር ታላላቅ የልማት ስራዎችን ማሳካት እንደሚችሉ ትምሀርት የሰጠ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡