ቀጥታ፡

በመጀመሪያ ዙር ጥሪ ከ74 ሺህ በላይ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት መጥተዋል- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2016(ኢዜአ)፦ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ጥሪን በመቀበል በመጀመሪያ ዙር ብቻ  ከ74 ሺህ በላይ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት መምጣታቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ታህሳስ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ  የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ጥሪው በዋናነት ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያንን ከአገራቸው ባህልና ታሪክ ጋር ማስተሳሰርን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ነብዩ ሰለሞን ለኢዜአ አንደገለጹት፤ ጥሪው በሶስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የተላለፈ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ''ከብዝሃ ባህልና ማንነት ጋር መገናኘት'' በሚል ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 30/2016 ዓ.ም መከናወኑን አስታውሰው፤ ይህም  የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን እንዲያውቁና እንዲጎበኙ ያደረገ ስለመሆኑ ጠቆመዋል፡፡

ጥሪውን በመቀበልም በመጀመሪያው ዙር ብቻ ከ74 ሺህ በላይ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መጥተዋል ነው ያሉት።  

ጥሪውን ተቀብለው ለመጡ ኢትዮጵያዊያን  በአገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በሚመለከት በተገቢው መልኩ የማስተዋወቅና የማስጎብኘት ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

ጥሪውን ተቀብለው የመጡት እንግዶችም አገራቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ በልማት ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት ቃል በመግባት ያረጋገጡበት በመሆኑ ቆይታቸው ስኬታማ እንደነበር አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛው ምዕራፍ ጥሪ በይፋ መጀመሩን ጠቁመው ጥሪው እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም  እንደሚቆይ ተናግረዋል፡፡

ጥሪው ''ታሪካዊ መሰረቶን ይወቁ'' በሚል እየተከናወነ ሲሆን፤ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ከአገራቸው ታሪክና ቅርስ ጋር የሚተዋወቁበት እድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡

የአድዋ ታሪክን መነሻ በማድረግ ለጉብኝት ክፍት የሆነው የአድዋ ሙዝየምን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶችን የሚጎበኙበት እድሎች ተመቻችተዋል ነው ያሉት።

ጎን ለጎንም ኢትዮጰያ ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በማስገንዘብ የሁለተኛው ትውልድ አባላትም በዘመናቸው የራሳቸውን አሻራ እንዲያኖሩ የሚያበረታታ ስለመሆኑም አብራርተዋል። 

        

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም