ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ከለውጡ በኋላ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ መስኮች ከፍተኛ ውጤቶች ተመዝግበዋል - አቶ ሃይሉ አዱኛ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ከለውጡ በኋላ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ መስኮች ከፍተኛ ለውጥ የታየባቸው ውጤቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ገለጹ።

በክልሉ ''ለሰላማችን ዘብ እንቆማለን ለውጡን እናጸናለን'' በሚል መሪ ሀሳብ ሰላማዊ ሰልፍ ይካሄዳል።

የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ሁሉም ዞኖች የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ከለውጡ በኋላ የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሰላማዊ ሰልፉ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል ከለውጡ በኋላ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ መስኮች ከፍተኛ ለውጥ የታየባቸው ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በፖለቲካ ረገድ ከለውጡ በኃላ በክልሉ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት በሰላማዊ መንገድ መታገል የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ኃላፊው አንስተዋል።

በኢኮኖሚ ረገድም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝምና በማዕድን ልማት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም በግብርና ልማት የክልሉ መንግስት የተለያዩ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮችን ቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱን ጠቅሰው በዚህም ከፍተኛ እምርታ መታየቱን ገልጸዋል።

በክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በሩዝ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተገኙ ውጤቶች መልካም ተሞክሮ የተገኘባቸው መሆኑንም አውስተዋል።

በማህበራዊ ልማት ዘርፍም በትምህርት፣ በጤናና ሌሎች የህዝቡን ችግር የሚፈቱ በርካታ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በትምህርት ልማት ብቻ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ስራዎች፣ የሁለተኛ ደረጃና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታም በስፋት መከናወኑን አብራርተዋል።

ዛሬ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የሩጫ ውድድሮች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም